በኦሮሚያ ምርት በንቅናቄ እንዲሰበሰብ ዕቅድ መዘጋጀቱ ተገለጸ

86
ኢዜአ ህዳር 13/2012  በአገሪቱ የወጣውን አየር ትንበያ መረጃ መሰረት በማድረግ በኦሮሚያ የደረሰ ምርት በንቅናቄ እንዲሰበሰብ ዕቅድ መዘጋጀቱ ተገልጿል። ይህንኑ አስመልክቶ የክልሉ ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በክልሉ በምዕራብ፣ በመካከለኛ፣ በደቡብ እና በሌሎች ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል መባሉን ተከትሎ የደረሰ ምርት በንቅናቄ እንዲሰበሰብ ዕቅድ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ ገልጸዋል። አቶ ዳባ ደበሌ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት በወለጋ፣ በቡኖ፣ በበደሌ፣ በሸዋ ዞኖች፣ ደቡብ ኦሮሚያ በቦረና፣ ጉጂና ሀረርጌ እና በአብዛኛው ዞኖች ዝናብ መኖሩን ከትንበያ መረጃ ተገኝቷል። ክልሉ ካለው የሰብል መረጃ በመነሳት ዘንድሮ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቅ የገለጹት አቶ ዳባ፤ ለዚህ ሲባል ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ተኩል የምርቱን መሰብሰቢያ መርሃ-ግብር ዕቅድ እስከ ቀበሌ አውርዷል። ስለሆነም ሁሉም ህብረተሰብ በተሰጠው መርሃ-ግብር መሰረት በባህላዊና በዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ዘዴ ተሳትፎ በማድረግ ከአርሶ አደሩ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል። በጥሪው መሠረትም እህል በሚሰበሰብበት ወቅት  ኮምባይነር የመሰለ ዘመናዊ መሳሪያ እና ደቦ መሰል ባህላዊ  የሰብል መሰብሰቢያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል። ሰብሉ ሲከማች፣ ሲጓጓዝ እንዲሁም እንደሰብሉ ተፈጥሯዊ ችሎታ ከብክነት በሚቀንስ አግባብ እንዲሰበሰብ ጥንቃቄ እንደሚደረግም በመጥቀስ። በሚወጣው የንቅናቄ መርሀ-ግብር አርሶ-አደሩን ጨምሮ የገጠርና ከተማ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ክልሉ በምርት ዘመን ለማረስ ከታቀደው 601 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ የዕቅዱን አፈጻጸም ከመቶ ፐርሰንት በላይ ማሳካት መቻሉ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም