በተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተመራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኡጋንዳ ያቀናል

114
ኢዜአ ህዳር 13/2012 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኡጋንዳ ያቀናል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በቀጣዩ ሳምንት ኡጋንዳ እንደሚያመራ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል። ዓላማውም የኢትዮጵያና ኡጋንዳን ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር ነው ብለዋል። ከህዳር 16 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቡድኑ በሚኖረው ቆይታ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና በአገሪቷ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል። ኡጋንዳ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2011 የፈረመችውን የናይል የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ባለፈው ሳምንት በፓርላማዋ እንዳጸደቀችም አስታውሰዋል። የኢትዮጵያና ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ዓላማ በማድረግ የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ትናንት ከኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው። የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታ የአንድነት ፓርክን፣ ብሔራዊ ሙዚየምንና የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ይጎበኛሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቴአትር በሚካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት የሚታደም ሲሆን የሱዳን ሙዚቀኞችም ስራቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም