የደቡብ ክልል አርሶ አደሮች ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል—ቢሮው

254

ሐዋሳ ኅዳር  12 / 201 የደቡብ ክልል አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብላቸው ላይ ጉዳት እንዳያይጎዳ ጥንቃቄ አንዲያደርጉ የክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አሳሰበ፡፡
አንበጣና የግሪሳ መንጋ ጥፋት ሊያደርሱ እንደሚችሉም ተመልክቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስገነዘቡት አርሶ አደሮቹ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሰብላቸው እንዳይበላሽ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል።

በዚሀም በወላይታ ፣ ከምባታ ጠምባሮ ፣ ዳውሮ ፣ ጋሞ ፣ ጎፋ ፣ ከፋ ፣ ቤንች ሸኮ ፣ ደቡብ ኦሞ ፣ ጌዴኦ ፣ ኮንሶ ፣ ከፊል ሀድያ ፣ ከፊል ጉራጌ ፣ ደራሼና ቡርጂ እንዲሁም ደጋማ የስልጤ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ባለፈው ሳምንት በካፊያ መልክ የጀመረው ዝናብ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፣ዝናቡ ሊጠናከር ስለሚችል ኅብረተሰቡ ሰብሉን ከጥፋት ለማዳን ርብርብ እንዲያደርግ  ጠይቀዋል።

በጉራጌ ፣ ስልጤ ፣ ሀላባና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም በቆላማ የሀዲያና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ወረዳዎች የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቢሮው ከኢትዮጵያ ግብርና ሜካናይዜሽን ማህበር ጋር በመቀናጀት ከ90 በላይ ኮምባይነሮችን በማስገባት የደረሰ ሰብል ለመሰባሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኮምባይነሮቹ አቅርቦት ከአርሶ አደሩ ፍላጎት፣ ወቅቱን ካልጠበቀዝናብና  ሌሎች ሥጋቶች ጋር

ተዳምሮ ኮምባይነሮች  ባልተዳረሱባቸው አካባቢዎች የሰው ኃይል  በማስተባበር የደረሰውን ሰብል በአፋጣኝ

እንዲሰበሰብ   አስገንዝበዋል፡፡

እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ የበረሀ አንበጣና የግሪሳ ወፍም በሰብሉ ላይ የተደቀኑ ሥጋቶች ናቸው ፡፡

በስድስት ክልሎች ላይ የተስተዋለው አንበጣ ባለመጥፋቱና ፍልሰቱም ባለመቆሙ በተለይ በደቡባዊ ድንበሮች ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ አብራርተዋል ፡፡

አርሶ አደሮች፣ የዕፅዋት ክሊኒኮችና የላቦራቷር ባለሙያዎች እንዲሁም የአስተዳደር አካላት በንቃት እንዲከታተሉትና ትኩረት እንዲሰጡት ምክትል ኃላፊው አስገንዝበዋል።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ገደማ  የተከሰተው የግሪሳ ወፍ ዳግም ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ መሰል ክስተቶች በሚታዩበት ወቅት ለሚመለከታቸው አካላት  እንዲያሳውቅ አመልክተዋል ፡፡

በክልሉ በ2011/12 የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደነበረና ካለፉት ዓመታት የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ የቢሮው መረጃ ያመለክታል።