የአፈር ጤንነትና ለምነት ተግዳሮትን ለመቀልበስ….

2114

ወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ)

በሀገር አቀፍ ደረጃ የአፈር ጤንነትና ለምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን  መረጃዎች ያሳያሉ።

ለችግሩ መከሰት በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ  የአፈር ለምነት እና ጤንነት ማሻሻያ ስራው በስትራቴጂ አለመመራቱ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

ችግር ፈቺ፣ ተስማሚና ዘላቂነት ያላቸው የአፈር ለምነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎችና አሰራር ዘይቤዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም እንዲሁ።

ስራዎችን አቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍና አደረጃጀት አለመኖርም ሌላኛው ተግዳሮት ነው።

ችግሮቹን  በዘላቂነትና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመፍታት  የአፈር ለምነት እና ጤንነት ስትራቴጂ ሰነድ መዘጋጀቱን ነው የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ያስታወቀው።

ሚኒስቴሩ ስትራቴጂውን ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት አግባብ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር በአዳማ ከተማ አውደ ጥናት አካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረበው  ሰነድ እንደሚያመለክተው  ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈር ጤንነትና ለምነት ማሻሻያ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በሚፈለገው ደረጃ  አልደረሰም።

ለውጤቱ አለመገኘት በዋና መንስዔነት ከተዘረዘሩት ውስጥ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ተግዳሮቶች መጠን፣ስፋትና ስርጭት በጥልቀት አለመታወቃቸው ቀዳሚ ነው።

ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማስተዋወቅና በማስረጽ ዙሪያ ያሉት የአሰራር ዘይቤዎችና ትስስሮች ከሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረስም ሌላኛው ማነቆ መሆኑንም ሰነዱ ያሳያል።

በመድረኩ ላይ ያገኘናቸው የግብርናና እንስስት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንደሚሉት ደግሞ በአፈር ጤናማነትና ለምነት ረገድ ካሉ ማነቆዎች መካከል የተፈጥሮ ማዳበሪያን በተገቢው ሁኔታና መጠን በስፋት ጥቅም ላይ አለማዋል ይጠቀሰል።

በአፈር መጎሳቆልና ብክለት ምክንያት የአፈር ምርታማነት መቀነስና ጤናማነት መታወክ እንዲሁም ዘርፉን የሚመራ ስትራቴጂ አለመኖር ሌላው ማነቆ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በመሆኑም በሚኒስቴሩ የተዘጋጀውና ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ስትራቴጂ ሰነድ በአፈር ጤናማነትና ለምነት ረገድ ያሉትን አቢይት ማነቆዎችን በመለየት መፍትሄዎችንም በዝርዝር ማስቀመጡን በማመልከት።

ሰነዱ ሲዘጋጅ የገጠር ልማት ስትራቴጂውን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ካባ በተቀናጀ የአፈር ጤንነትና ለምነት ማሻሻያ ስራዎች አፈጻጸም ያጋጠሙ ዋና ዋና ክፍተቶችንም ታሳቢ አድርጓል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ ስትራቴጂው ስራ ላይ ሲውል በአፈር ጤንነትና ለምነት  ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የአፈር አሲዳማነት በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል።

ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉልና አማራ ክልሎችን ጨምሮ በሀገሪቱ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሰፊ አሲዳማ አፈር ለማካም፣ የኖራ አቅርቦቱን ቅልጥፍናና ውጤታማነት ለመጨመር ስትራቴጂው ወሳኝ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የአፈር አሲዳማነት መስፋፋት በሀገሪቱ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት  በሰብል እንዳይሸፈን ማድረጉን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ለእርሻ ከሚውለው 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታሩ ለምነቱን አጥቷል።

በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳው የተፈጥሮ ሀብት እንዲያገግምና በዘላቂነት እንዲጠበቅ የመንግስትን የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የተቀረጸ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ስትራቴጂው በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸውን የአፈር ጤንነትና ለምነት ማነቆዎችንና የመፍትሄ ሃሳቦችን ዘርዝሮ መያዙን በማመልከት።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉትም ስትራቴጂው በመላ ሀገሪቱ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ዓመታት ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።

በዋናነት በአነስትኛ ማሳ ላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢያሱ አብርሃ በሰጡት አስተያየት ”በተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራችን በተለይም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ ያስመዝገብነው የላቀ ስኬት በዓለም ደረጃ ዕውቅና አስገኝቶልናል” ብለዋል።

የአፈር ጤንነትና ለምነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎችንና የአሰራር ዘይቤዎችን በማላመድ፣በማስተዋወቅና በማስፋፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የስምንት በመቶ የምርትና ምርታማነት እድገት ለማሳካት ስትራቴጂው ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የስትራቴጂው ሰነድ የተዘጋጀው ዩኒቨርስቲዎችን፣ የፌዴራልና የክልል ግብርና ምርምር ተቋማትን እንዲሁም በአፈር ለምነት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን በማሳተፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን ናቸው።

ስትራቴጂው ከአፈር ለምነትና ጤንነት አኳያ ያጋጠሙ ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ ማነቆዎችን በመለየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለይቷል ይላሉ።

የስነ ምህዳርን፣ የአፈር ዓይነትን፣ የመሬት አቀማመጥንና የሰብል አመራረት ስርዓትን መሰረት ያደረጉ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊነትን ከማጉላት ባለፈ ተስማሚ የግብዓት አቅርቦት፣ ስርጭትና ተደራሽነትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈን እንደሚያስችል ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

በየደራጃው የሚገኙ አስፈፃሚ አካላትን የማስፈጸም አቅም በመገንበትና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትስስርን በማጠናከር በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የጎላ ሚና አለው ባይ ናቸው።

ስትራቴጂው ወደ ክልሎች ወርዶ እንዴት የ2011 ዓ.ም የእቅዳቸው አካል አድርገው ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን በመጠቆም።

በስትራቴጂ ሰነድ ዝግጅቱ  ከተሳተፉት አካላት መካከል የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ የአፈር ሣይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዋሴ ሃይሌ አንዱ ናቸው።

ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ የሰብል ምርታማነት እንዲቀነስ ካደረጉት ቁልፍ ነገሮች መካከል የደን መጨፍጨፍ፣ መሬት በተደጋጋሚ መታረስና የአፈር ጤንነት መጓደል ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ ለመከላከል፣ የአፈር ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ቅንጅታዊ አሰራርን ለማስፈን፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ስትራቴጂው ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለተግባራዊነቱ ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል ባይ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሸለማ አማና ስትራቴጂው የአርሶና አርብቶ አደሩን ሰፊ ጉልበት ከዘመናዊ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለማስተሳሰርና ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓትን ለማስፈን ይረዳል ነው ያሉት።

ይህም ድርቅን በመቋቋምና የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት የማረጋገጥ ግቡ እንዲሳካ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።