አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከሱዳን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር ተወያዩ

87

ኢዜአ፤ ህዳር 12/2012 የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማደረግ ላይ የሚገኘውን የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንን ዛሬ ተቀበለው አነጋግረዋል።

አፈጉባኤው ልኡካን ቡድኑን “ወደ ሁለተኛ አገራችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት፣ በመልካምም ሆነ በችግር ጊዜ ያልተቋረጠውን የሱዳን ህዝብ እውነተኛ ወዳጅነትን አመስግነዋል።

“ከሱዳን ወንድሞቻችን ጋር ስንወያይ እንደ ሁለት አገር ዜጎች ህዝቦች ሳይሆን በአንድ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ቤተሰቦች ነው የሚሰማን” ነው ያሉት አፌ ጉባኤው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው “ከአንድ ወንዝ የሚጠጡት የሁለቱ አገር ወንድም ህዝቦች” ወዳጀነት ለዘመናት የዘለቀና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እና እያደገ መምጣቱን ገለጸዋል።

በሱዳን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በውይይት ተፈትቶ የሽግግር መንግስት መመስረቱ ሱዳናዊያን ችግራቸውን በራሳቸው ለመፍታት ያላቸውን ችሎታ ያሳያልም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሽግግር መንግስቱ ምስረታ ላይ በተገኙበት ወቅትም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

ከዚህም ባሻገር ከሜሮዬ እና ከአክሱማዊት ጊዜ ጀምሮ የንግድ ግንኙነት ያላቸው እነዚህ ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚ ዙሪያ ያላቸውንም ትስስር ይበልጥ አጠናክረው ለመቀጠል ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልኡካን ቡድን መሪ የሆኑት የሱዳን ህዝቦች ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ምክር ቤት ሴክሬታሪ ጀነራል ሳልዋ ሞሃመድ ማህጁብ በበኩላቸው በአፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል።

 

የዚህ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አላማም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሱዳን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ወገኖችን ቀርበው በማነጋገር ልዩነታቸውን እንዲፈቱ እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዲመጣ ላደረጉት አስተቀዋዕጾ ምስጋናቸውን ለማቅረብ እንዲሁም በሁለቱ አገራት ህዘቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለአለም ለማሳወቅ እንደሆነም ነው የገለጹት።

ልኡካን  ቡድን መሪ ሳልዋ ሞሃመድ ማህጁብ በማያያዝም የሱዳን የሽግግር መንግስት ከተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ የመጀመሪያ ጉብኝቱን በኢትዮጵያ ማድረጉ የሁለቱን አገር ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት የደረሰበትን ከፍተኛ ትስስር የሚያሳይ ነውም ብለዋል።

የሁለቱ አገሮች የወዳጅነት ማህበሮች እንዲጠናከሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲያድግ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የባህል ትስስሩ እንዲጠናከር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡደኑ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንም ተመሳሳይ ጉብኝት በሱዳን እንዲያካሂድ በዚሁ ወቅት መጋበዛቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም