በቢራ ገብስ መሰማራታችን ተጠቃሚ አድርጎናል - የአጎለላና ጠራ ወረዳ አርሶ አደሮች

159
ደብረ ብርሃን ሰኔ 14/2010 በቢራ ገብስ ልማት ተሰማርተው የሚያገኙትን ምርት ለብቅል ፋብሪካ በማቅረብ እስከ 32 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን በሸዋ ዞን የአጎለላና ጠራ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። በዘንድሮው የመኸር እርሻ 6 ሺህ ሄክታር መሬት በቢራ ገብስ ለመሸፈን የእርሻ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል። በወረዳው የሰሪቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድወሰን ወልደሐና ለኢዜአ እንደገለፁት ለዘመናት ባካሄዱት የግብርና ስራ የምግብ ገብስ ሲያመርቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ከልማቱም ከአንድ ሄክታር መሬት ከዘጠኝ ኩንታል የማይበልጥ ምርት ይሰበስቡ እንደነበር አስታውሰዋል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቢራ ገብስን ማዳበሪያን በመጨመርና በመስመር በመዝራት ባለፈው ዓመት ብቻ በሄክታር 23 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልፀዋል። ያገኙትን የቢራ ገብስም ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ በማስረከብ ከ32 ሺህ 200 ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም 2 ሄክታር ተኩል መሬት በቢራ ገብስ በዘር ለመሸፈን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በወረዳው ቡራና ጦጦሴ ቀበሌ አርሶ አደር ካሊድ ሙሄ በበኩላቸው በቀዳሚው ዓመት ከሩብ ሄክታር መሬት አምስት ኩንታል የቢራ ገብስ ምርት አምርተው በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። የቢራ ገብስ በገበያው ላይ አዋጪና የተሻለ የገበያ አመራጭ ያለው በመሆኑ ዘንድሮ በኩታ ገጠም ተደራጅተው አንድ ሄክታር መሬታቸውን በዘር በመሸፈን ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ገልጠዋል። በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው በበኩላቸው አርሶ አደሮች ከምግብ ሰብል በተጓዳኝ በገበያ አዋጪ የሆነ የቢራ ገብስ  በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በቢራ ገብስ ልማቱም በ45 ቀበሌዎች የሚገኙ 17 ሺህ 522 አርሶ አደሮች በቢራ ገብስ ክላስተር ተደራጅተው ልማቱን እያከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል። በ2009/2010 በተካሄደው የቢራ ገብስ ልማትም 3 ሺህ 390 ሄክታር መሬት በማልማት 74 ሺህ 523 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ አብዛኛውን ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል። በዚህ የክረምት ወቅትም 6ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስካሁን 1 ሺህ 582 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልፀዋል። በዘር ከሚሸፈነው መሬትም 136 ሺህ 524 ኩንታል የጥራት ደረጃውን ያሟላ የቢራ ገብስ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም