በምስራቅ ሐረርጌ ሰባት ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ መቆጣጠር ተቻለ

71
ኢዜአ ህዳር 12/2012 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሰባት ወረዳዎች  የተከሰተው የአንበጣ መንጋ መቆጣጠር መቻሉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የሰብልና አዝዕርት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ዘለቀ አብደታ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአንበጣ መንጋው በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎቹ ውስጥ ተከስቶ ነበር። በወረዳዎቹ  62 ቀበሌዎች  የተከሰተው የአንበጣ መንጋም 23ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የሚገኙ ሰብል፣ግጦሽ፣ደን፣ሳርና ሌሎች እጽዋቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል። በአሁኑ ወቅትም የአንበጣው መንጋ ከተከሰተባቸው ዘጠኝ ወረዳዎች መካከል በሰባቱ  መቆጣጠር ተችሏል። ቡድን መሪው እንዳሉት ለመቆጣጠርም  ከ32ሺ በላይ  ተማሪዎች፣አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ባህላዊ ዘዴ ተሳትፈዋል። የአንበጣ መንጋው ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው ቀሪዎቹ ጭናክሰንና ቀርሳ ወረዳዎች  840 ሊትር ኬሚካል በአውሮፕላን የመርጨት ስራ መከናወኑን አቶ ዘለቀ አስረድተዋል። በእነዚህ ወረዳዎች የመከላከሉ ስራ  አሁንም እንደቀጠለ ነው። በአሁኑ ወቅት የአንበጣው መንጋ እንቁላል የጣለበትን ስፍራ ዳግም እንዳይፈለፈል በባለሙያ የታገዘ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በጃርሶ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የአዝዕርት ባለሙያ አቶ ተስፋዬ አሰፋ  በበኩላቸው በአካባቢያቸው የተከሰተው  የአንበጣው መንጋ  3ሺ  ሄክታር መሬት  የሸፈነ  ሰብል፣የእንስሳት  መኖና የደን ዛፍ  ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። አርሶ አደሩና ሌሎም የህብርተሰብ ክፍል በባህላዊ ዘዴ በመከላከል መቆጣጠር እንደተቻለም ባለሙያው  አመልክተዋል። ተመልሶ እንዳይመጣም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም