በህጻናት ላይ የሚስተዋለው የአእምሮአዊ እድገት ችግር ለማቃለል የሚያስችል የምርምር ማዕከል ሊቋቋም ነው

89

ህዳር 12/2012 በአማራና ትግራይ ክልሎች በተመጣጠነ የምግብ ስርዓት መጓደል በህጻናት ላይ የሚስተዋለውን አካላዊና አእምሮአዊ እድገት የጤና ችግር ለማቃለል የሚያስችል የምርምር ማዕከል ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ፡፡

ማዕከሉ በተከዜ ተፋሰስ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ 33 ወረዳዎች በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ያከናውኗል።

በምዕራብ በለሳ ወረዳ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ጀግናው ክብሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የምርምር ማዕከሉ የህንጻ ግንባታ ዘንድሮ  ተጀምሮ በአንድ ዓመት በማጠናቀቅ ስራ ይጀምራል።

ዓለማውም ተፋሰሱ በሚያቅፋቸው ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ልማዳዊ የስርዓተ ምግብ አጠቃቀምን በማሻሻል በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን ለህጻናት እንዲመግቡ እገዛ  ማድረግ ነው፡፡

ማዕከሉ በግብርናው ዘርፍ ምርታማ የሆኑና በንጥረ ነገር ይዞታቸው የበለጸጉ አትክትልና ፍራፍሬዎችን በማላመድና በማስተዋወቅ በአካባቢዎቹ  በስፋት የሚለማበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡

በዚህም በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍም ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በማደቃልና ዘመናዊ የእንስሳት ማድለብ ቴክኖሎጂን በማስረጽ ህጻናት በፕሮቲን የበለጸገ ስጋና ወተት እንዲመግቡ ያደርጋል፡፡

አስተባባሪው “ዘመናዊ የዓሳ እርባታን ዘዴ በማስፋፋት፤ በማላመድ ህብረተሰቡ ለታዳጊ ህጻናት ዓሳ የመመገብ ባህሉን እንዲያጎለብት በምርምር የተደገፉ ተግባራት ይከናወናሉ “ብለዋል፡፡

“ማዕከሉ የእስራኤልን የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ አካባቢዎቹ በማምጣት ሰፊ የማላመድ ስራ ያከናውናል “ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሙላት ተካ ናቸው፡፡

ከሀገር ውሰጥ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀትም በምርምር የፈለቁ የሰብል ፣የእንስሳት፣ የጓሮ አትክትና ፍራፍሬዎችን ወደ አካባቢዎቹ በማምጣት ለአርሶአደሩ በስፋት እያስተዋወቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

አቶ ሙላት እንዳሉት ማዕከሉ አዳዲስ የግብርና ፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በተፋሰሱ የሚገኙ አርሶአደሮች በንጥረ ነገር የበለጸጉ የሰብል ምርትና የእንስሳት ተዋጽኦ በስፋት አምርተው ልጆቻቸውን እንዲመግቡ እገዛ ያደርጋል፡፡

ለመርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያም በመንግስት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንም አመልክተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ የሚቋቋመው የምርምር ማዕከሉ በተከዜ ተፋሰስ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ 33 ወረዳዎች   በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ያከናውናል ተብሏል።