ደቡብ ወሎ ዞን በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 400 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ

64
ደሴ ኢዜአ ህዳር 12 ቀን 2012 ዓም  በደቡብ ወሎ ዞን ለልማት የሚያስፈልገውን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን የተቀናጀ የግብር አሰባሰብ ስራ እየተካሔደ መሆኑን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ አሰታወቀ። መምሪያው በዓመቱ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየተረባረበ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ አራት ወራት 400 ሚሊዮን ብር እንደሰበሰበ አስታውቋል ። በገቢ አሰባሰብ፣ ባጋጠሙ ችግሮችና በተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር የተደረገበት መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሔዷል ። የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ጉልላት ወርቁ እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ የዞኑ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን 1 ነጥብ 2  ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል። በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብም ለልማት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ 29 በመቶ በራስ አቅም ለመሸፈን ታልሞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ አካባቢ በተካሄደ የተቀናጀና የተደራጀ ርብርብ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አስረድተዋል። ግብሩን መሰብሰብ የተቻለውም ከ40 ሺህ ግብር ከፋዮች መሆኑን ጠቁመው ከ98 በመቶ በለይ የሚሆኑት የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ያለ ቅጣት በወቅቱ መክፈላቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል ። ዞኑ ለጂቡቲ ወደብ ቅርብ መሆኑ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩ፣ ለግብርና ምቹ መሆኑንና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያፋጥኑ መደላድሎች መኖራቸው ከእቅድ በላይ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አስረድተዋል ። ይሁን እንጂ የሐሰት ደረሰኝ መስጠት፣ ደረሰኝ አለመስጠትና አለመቀበል፣  ማጭበርበር፣ የፖለቲካው አለመረጋጋት፣ህገ ወጥ ተግባራት መበራከትና ሌሎች ተግዳሮቶች ለገቢ አሰባሰቡ ፈታኝ መሆናቸውን ገልፀዋል ። ችግሩን ለመቅረፍ ተመሳሳይ መድረኮች  በማዘጋጀት ከአመራሩና ህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸው ተናግረዋል ። ህብረተሰቡ የሚሰበሰበው ግብር ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች ማሟያ መሆኑን አዉቆ አገራዊ ግዴታውን መወጣትና መብቱንም ማስከበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በወረኢሉ ከተማ በእህል ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ሰይድ አሊ በሰጡት አስተያየት በሚሰሩት ልክ ግብር በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን መወጣት በመቻላቸው የህሊና እርካታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል ። በዚህ  ዓመት ከ75 ሺህ ብር በላይ ግብር መክፈላቸንን የተናገሩት አቶ ሰይድ ህብረተሰቡን በማሳመን ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ግብር እንዲሰበሰብ የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ ብለዋል ። በግብር አሰባሰቡ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎችና አመራሩ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ በኮምቦልቻ ከተማ በአስመጭና ላኪ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ዳዊት ታደሰ ናቸዉ፡፡ ሐሰተኛ ደረሰኝ በሚጠቀሙ ፤ ግብር በሚጭበረብሩና በህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ረገድ መንግስት ኃላፊነቱ እየተወጣ አይደለም የሚል ቅሬታ እንዳላቸው ባለሃብቱ ተናግረዋል ። የሀገር ፍቅር የሚገለጸው በወሬ ሳይሆን በተግባር ነው ያሉት አቶ ዳዊት በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግብር በመክፈል ግዴታቸውን በታማኝነት እየፈፀሙ መሆናቸውን ገልፀዋል ። የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ተወካይ አቶ ፍቅረማሪያም ደጀኔ በበኩላቸው የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ግብር መሰብሰብ ያስፈልጋል። በተለይ በክልሉ የሚስተዋለውን የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ ህብረተሰቡ በሰራው ልክ ግብር እንዲከፍል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በክልል ደረጃ ለመሰብሰብ ከታቀደዉ 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ዉስጥ እስከ አሁን ድረስ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም