የአልጀርሱ ስምምነት ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ ይደረጋል—ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

3602

መቀሌ ሰኔ 14/2010 የአልጀርሱን ስምምነት ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ በሁለቱ ሃገራት ድንበር መካከል የቆየውን ዝምታ የሰበረ መሆኑን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ገለጹ።

መንግስት እወስደዋለሁ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያም የልማታዊ መንግስትን ፖሊሲ የሚቃወም እንዳልሆነ አመልክተዋል።

ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት ስምምነቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር ያስችላል።

ግጭቱ በድንበር አካባቢ ሊካሔድ የሚገባውን ልማት ከማደናቀፉም ባለፈ በሁለቱም ሃገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጰያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችም ከልማትና ከስራ ውጭ ሆነው በጸጥታ ስራ ላይ እንዲውሉ ማስገደዱን ጠቁመው አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ለ18 ዓመታት የቆየውን ዝምታ የሰበረ መሆኑን አስረድተዋል።

አፈጻጸሙም ከመንግስታቱ ባለፈ የሁለቱን  ሃገራት ህዝቦች ተጠቃሚነትና ይሁንታ ባረጋገጠ መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ቀደም ሲል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል በማስታወቁ በህዝቡ ላይ የተፈጠረውን መደናገር ለማስቀረት ከመግለጫው በፊት ህዝቡ እንዲረዳው መደረግ እንደነበረበት ተናግረዋል።

ውሳኔውን ተከትሎም የኤርትራው ፕሬዝዳንት መልዕክተኞችን ለመላክ መዘጋጀታቸውን በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ጠቁመው የአልጀርሱ ስምምነትም ከነሙሉ ማዕቀፉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ምክትል ርእሰ-መስተዳደሩ አያይዘው እንደገለጹት መንግስት ባቀደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት በእጁ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል እንዲዛወሩ መወሰኑ ከልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ጋር የሚጋጭ አይደለም።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከዓመት በፊት በጥልቀት እንደተወያየበት ገልጸው ይህ ሃገሪቱን ለገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈጣን ምላሽ ስለማይሰጥ ህገ-ወጥና ኮንትሮባንድ ንግዶችን ማስቆም ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።