ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መፍትሔ

82

ያንተስራ ወጋየሁ ዲላ ኢዜአ

ኢትዮጵያ የግልን ጨምሮ ከ70 የሚልቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ ።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ቀዳሚ አጀንዳቸው ነው ። ችግር ፈቺ ምርምሮችና ጥናቶችን በማካሔድ የአካባቢውን ማህበረሰብ ክፍተት በመሙላት የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ደግሞ ተሰፍሮ ከተሰጣቸው ሃላፊነቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ።

ከተጣለባቸው ሀገራዊ ሃላፊነት አንጻር እያስገኙት ያለው ውጤት ግን አበረታች ነው ለማለት አያስደፍርም።

ለዚህም የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮ የሆነውን በስነ ምግባር የታነጸ ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራት ሂደቱን መውሰድ ጥሩ ማሳያ ነው።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በመሰልጠን ላይ ያለውም ሆነ ሰልጥኖ የወጣውን ሀይል ሀገራዊ ሁኔታን በሚገባ ተረድቶና ቀጣይ አዝማሚያዎችን ተንትኖ የመረዳትም የማስረዳት አቅሙ ደካማ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁሟሉ።

በመንጋ አስተሳሰብ በውል ባልተረዳው አጀንዳ የመሳተፍ እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ያስጠናውን ጥናት ጨምሮ በርካታ ግኝቶች ጠቁመዋል ።

ችግሩን ከዚህም በላይ ውስብስብ የሚያደርገው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀገራዊ ሃላፊነት ከመወጣት አንፃር ግማሽ መንፈቅ ዓመት እንኳን በሰላም ማጠናቀቅ ሲያቅታቸው ይስተዋላል ።

በተለይም ሀገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቱ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ በመግባት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማወክና ከማስተጓጎል ባለፈ የሰው ሕይወት ጭምር የሚጠፋበት አጋጣሚ መከሰቱ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን ተቋማቱ ከፀጥታ ስጋት ነጻ እንዲሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ተጨባጭ ለውጥ ግን ማምጣት አልተቻለም ።

ይሁንና የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑ ይበል የሚያስብል ነው።

ተቋማቱም ቢሆኑ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ ከጸጥታ ስጋት ነጻ ለመሆን በየፈርጃቸው ሲጥሩ ማየትና መስማት የተለመደ ሆናል ። ለዚህም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ለ5 ሺህ ተማሪዎች 5 ሺህ ወላጅ ፕሮጀክትን መተግበሩ ጥሩ ማሳያ ነው።

ከሰሞኑንም የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን በዘላቂነት ሰላማዊ እንዲሆንና በስነ ምግባር የታነጸ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር አጋዥ ይሆናል ያለውን የገዳ ስርዓት ትምህርት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ብዙ የጸጥታ ችግሮችን አሳልፈናል የሚሉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ በተለይ በተጠናቀቀው ዓመት የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ባጋጠመው የጸጥታ ችግር የመማር ማስተማር ሂደቱ ለሳምንታት ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል

ባለፉት አመታት ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍና በዩኒቨርሲቲው ሰላም ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት ቢከናወኑም የተፈለገውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ያስረዳሉ ።

ሃገሪቷ ለሰላም ግንባታ ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው በርካታ ባህሎችና እሴቶች ባለቤት ሆና ስታበቃ ሁሌም ለችግሮቻችን መፍቻ ከባህር ማዶ መጠበቃችን የተፈለገው ውጤት እንዳይመዘገብ የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳደሩን በማንሳት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ

ዩኒቨርሲቲው ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መፍትሔ ለመስጠት በማሰብ ለዘላቂ ሰላም ተስፋ የተጣለበት የገዳ ስርዓት ትምህርትን በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች ለመስጠት ወስኖ ወደ ተግባር መግባቱን ፕሬዚዳንቱ ያወሳሉ ።

የገዳ ሰርዓት ለሰላምና በጋራ ለመኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው እሴቶች ባለቤት ነው የሚሉት ዶክተር ጫላ ዋታ ስርዓቱ አንድነትን በማረጋገጥ መደማመጥና መከባበርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ አለመግባባትን ቁጭ ብሎ በንግርር መፍታትን ያስተምራል ። ይህንንም ለተማሪዎች በማስተማር አለመግባባት ተፈጥሮአዊ መሆኑንና በንግግር ብቻ እንደሚፈታ በማስገንዘብ በተቋምም ሆነ ከተቋም ውጭ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል ።

በተለይ ብቁና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለመፍጠር አጋዥ ከመሆኑም ባለፈ ለዘላቂ ሰላም ሀገራዊ መፍትሔ መሆኑን አብራርተዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የተወጣጡ የአካባቢውን ህብረተሰብ ያሳተፈ የመማክርት ምክር ቤት አቋቁሞ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን በቅርበት መከታተሉ የገዳ ስርዓት ትምህርት መስጠት ከመጀመሩ ጋር ተዳምሮ ተስፋ ሰጪ የሰላም ጭላንጭ እንዲታይ አድርጓል ።

በተማሪዎች የእርስ በርስ ግኑኝነትና ስነ ልቦና ላይ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣትም የተረጋጋ ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠሩንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የገዳ ስርዓት ምክር ቤት ሰብሳቢ አባጋዳ ጅሎ ማኖ በበኩላቸው በገዳ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ ፋይዳ ያለቸው እሴቶችን በተለይም ሰላም ፣በጋራ መኖርንና ችግሮችን በንግግር የመፍታት ልምዶች የወቁቱን ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየር የማይተካ ሚና አላቸው ሲሉ ተናግረዋል ።

በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶችን የነገ ሀገር ተረካቢ በመሆናቸው በግብረ ገብና በእውቀት ታንጸው እንዲወጡ ሀገር በቀል እወቀቶችን በማሸጋገር በኩል ሁሉም አካል በትኩረት መስራት እንዳለበት መክረዋል ።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ሰርዓት ትምህርት መስጠት መጀመሩ በዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጎን ለጎን ሀገራዊ እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ጠቀሜታው የላቀ ነው ።

አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቅርበት ከመስራት ጎን ለጎን ተማሪዎች በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የሚወስዱትን የገዳ ስርዓት ትምህርት በተግባር ለማወቅ ከፈለጉ በአባ ገዳዎችን ተገቢውን ድጋፍ ይደረግላቸዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የ3ኛ አመት የጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህረት ክፍል ተማሪ ማርታ ጅኖ በበኩሏ ከፍተኛ የትምሀርት ተቋማት ከፀጥታ ስጋት ነጻ ለማድረግ የተማሪዎችን አመለካከት ላይ መስራት ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት ትላለች ።

በተለይም በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶችንና ባህሎችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ መምጣት ወጣቱ ጠቀሜታቸውን በቅጡ ካለመረዳት የመጣ ችግር ነው ባይ ነች ።

በዚህ ረገድ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የገዳ ሰርዓት ትምህረት ስለ ሰላምና አንድነት ያላትን ግንዛቤ እንዳሳደገው ጠቁሟለች።

ሌሎች ተቋማትም በአካባቢያቸው ያለውንና ሁላችንንም በሚያግባቡ ሀገር በቀል እውቀቶች በመታገዝ የተማሪዎችን አመለካከት ለመቀየር መስራት አለባቸው የሚል መልእክት አስተላልፈላች ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም