ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን ጀመረ

121
ኢዜአ ህዳር12/2012 የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን ዛሬ መጀመሩን ፕሬዚዳንቱ አስታወቁ። ፕሬዘዳንቱ ዶክተር ጀጃው ደማሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ለአንድ ሳምንት ያህል ተስተጓጉሎ የቆየውን ሥራውን ቀጥሏል። ዩኒቨርሲቲው ሥራውን የቀጠለው የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዞኑ አስተዳደርና የጸጥታ ኃይሉ ባደረጉት ትብብር መሆኑን አስረድተዋል። አካላቱ የእርቅ መድረኮችን በማመቻቸት ተማሪዎችን በማስታረቅና በማስማማት ሚና መጫወታቸውንም ገልጸዋል። በዚህም በደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ተጠልለው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምሀርት ገበታቸው ተመልሰዋል ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ተማሪዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ትናንት የዩኒቨርሲቲውን ግቢውን ማጽዳትና ማስዋባቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው አለመረጋጋት ሁለት ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሥራ በማወክ የተጠረጠሩ ተማሪዎችን በሕግ አግባብ አጣርቶ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ዶክተር ጀጃው ተናግረዋል፡፡ ከተመሰረተ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ከ2ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ነው፡፡ በአራት ኮሌጆችና 22 የትምህርት ፋካልቲዎች የተደራጀው ዩኒቨርሲቲ ፣ ከ180 በላይ የመጀመሪያ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ መምህራን አሉት፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም