የኢህአዴግ ምክር ቤት የፓርቲውን ውህደት አፀደቀ

109
ኢዜአ ህዳር 11/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመራለትን የፓርቲውን ውህደት አፀደቀ። የምክር ቤቱ ስብሰባ በዛሬ ውሎው ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶችን በማዋሃድ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርጎ ከተወያየ በኋላ ነው ያጸደቀው። ኢሕአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ግንባሩ ከአጋሮቹ ጋር እንዲዋሃድና ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ እንዲሆን ሰሞኑን በአብላጫ ድምጽ በመወሰን ለምክር ቤቱ መምራቱ ይታወሳል። ውህዱ ፓርቲ "ብልፅግና ፓርቲ" የሚለውን ስያሜ ተሰጥቶት ለኢሕአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከስምምነት መድረሱም ይታወሳል። ምክር ቤቱም ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው ግንባሩና አጋር ድርጅቶቹ እንዲዋሃዱ ውሳኔውን አሳልፏል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ የዛሬውን የምክር ቤቱን ውሎ በማስመልከት ለኢቢሲ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በፓርቲው ውህደት ዙሪያ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። አቶ ፍቃዱ እንደገለጹት ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቶ ከመከረ በኋላ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ ነው ያጸደቀው። በውይይቱ ላይ የኢህአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም የውህደቱን አስፈላጊነት፣ ሕጋዊ አሰራርና ከደንቡ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት ማቅረቡን ነው የገለጹት። በኮሚሽኑ ጥናት ውጤት መሰረትም ኢህአዴግ አገራዊ ለውጡን ለመምራትና መሰረት ለማስያዝ፣ እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ተደርሷል። የውህደቱ ሂደትም ህገ ደንቡና ስርዓቱን የተከተለ መሆኑ ተረጋግጦ ምክክር ከተደረገበት በኋላ መጽደቁን አብራርተዋል። ምክር ቤቱ በሁለተኛ ደረጃ የተመለከተው “የብልጽግና ፓርቲ” ፕሮግራምን ሲሆን፤ ፓርቲው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በውጭ ግንኙነት ላይ የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በሰፊው መመልከቱን አብራርተዋል። ቀደም ብሎ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፓርቲው በመተዳደርያ ደንቡ ላይ በአገሪቷ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል። ውህዱ ፓርቲም አማርኛን ጨምሮ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ለስራ ቋንቋነት የተመረጡ መሆኑንም ማስታወቁ ይታወሳል። ብልፅግና ፓርቲ በፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር የሚሉትን ስያሜዎችን ይተካል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም