የኢጋድ መሪዎች በደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ሊመክሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ መሪዎች በደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ሊመክሩ ነው

አዲስ አበባ 14/2010 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ በደቡብ ሱዳን የሠላም ጉዳይ ላይ በመሪዎች ደረጃ የሚያደርገው ስብሰባ ከሰዓታት በኋላ ይጀመራል። ስብሰባው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ዳግም ገቢራዊ እንዲሆን በኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀደም ሲል የቀረበውን የሠላም ኃሳብ እቅድ ተቀብሎ ያጸድቀዋል ተብሏል። ሰነዱ በደቡብ ሱዳን ከሁለት ዓመታት በፊት ዳግም የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ኢጋድ በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ወይይት ካደረገበት በኋላ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል። ለአብነትም የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ስድስት አስቸኳይ ስብሰባና ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ ምክክሮች ማድረጉን ጠቁሟል። የቀረበው የሰላም ኃሳብ እቅድ ከዚህ ቀደም ከነበረው ይዘቱ ላይ በሁለቱም ጎራዎች የሚነሳውን አስተያየት በማካተት መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑ ተገልጿል። ይህም ደግሞ በተቀናቃኞች መካከል ያለውን አለመግባባትና ውጥረት በማርገብ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እውን ለማድርግ መሆኑም ተገልጿል። በመሆኑም ዛሬ በመሪዎች ደረጃ የሚካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ይህንን ሰነድ በማጽደቅ በአገሪቱ ሰላም አንዲሰፍን በማድረግ ታሪካዊ ይሆናል ነው የተባለው። ያም ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ በማስቀመጥም ሰብሰባው ሚናው የጎላ መሆኑን ከወዲሁ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ዛሬ ማለዳ ላይ የተጀመረው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባው ለመሪዎቹ ከዚሁ ውጪ ሌሎች የውሳኔ ኃሳብ ለመሪዎቹ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።