የኢትዮጵያና ጅቡቲን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያፈጥን የባለሙያዎች ውይይት በአዲስ አበባ ተጀመረ

78
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 የኢትዮጵያና ጅቡቲን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን ያለመ የባለሙያዎች ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ለሁለት ቀናት የሚቆየው የኢትዮጵያና የጅቡቲ የጋራ የባለሙያዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ዛሬ ተጀምሯል። ውይይቱን የከፈቱት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር መሀመድ ድሪር በውይይቱ ሁሉም የትብብር ዘርፎች የተገኙ ስኬቶችና ውስንነቶች ትኩረት ይደረጋል። የባለሙያዎቹ ውይይት የኢኮኖሚ ውህደቱን ለማፋጠንና ለማጎልበት ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል። ሁሉንም የትብብር ዕድሎች በመጠቀም የሁለቱም አገራትን ግንኙነት ለማጎልበትና የጋራ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የባለሙያዎቹ ውይይቱ ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል። የጅቡቲው የልኡካን ቡድን የመሩት ያሲን ሑሴን ዱዋሎ በአሁኑ ወቅት በሁሉቱም አገሮች ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን በመግለፅ የኢኮኖሚ ውህደቱን ለማፋጠን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በውይይቱ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የተደረጉ ስምምነቶችና የተሰሩ ሥራዎች በጥልቀት እንደሚገመገሙ ተገልጿል። የአገራቱ ግንኙነት በፖለቲካ፣ የደህንነት፣ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚና የትራንስፖርት  ዘርፎች ሪፖርቶች ቀርበው ባለሙያዎቹ በሶስት ቡድን ተከፍለው ጥልቀት ያለው ግምገማ ያደርጋሉ። የባለሙያዎቹ ውይይት የኢኮኖሚ ውህደት ሂደትን የሚያፋጥኑ ሓሳቦችን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም አዲስ የትብብር ዘርፎች ማየትና የማስፋት ዓላማም የውይይቱ  አካል መሆኑን ተናግረዋል። የሁለቱም አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን በፈረንጆች በ2016 በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ የስምምነቶችና ትብብሮች ተፈፃሚነት በየወሩ የሚገመግም የጋራ የባለሙያዎች እንዲኖሩ ተስማምተው ነበር። በዚሁ መሰረት በዛው ዓመት መጨረሻ የመጀመሪያው የጋራ ባለሙያዎች ስብሰባ በጅቡቲ ሲካሄድ ሁለተኛው የባለሙያዎቹ ስብሰባ ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም