በአገሪቱ በቅርቡ 5ኛው ትውልድ (5ጂ) የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ይተዋወቃል

75

ኢዜአ፤ ህዳር 11/ 2012 ኢትዮጵያ በቅርቡ 5ኛው ትውልድ (5ጂ) የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን ልታስተዋውቅ መሆኑ ተገለፀ።

በአፍሪካ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትና የተንቀሳቃሽ ስልክ ግብይት ላይ የሚነጋገር ስብሰባ በአዲስ አበባ  እየተካሄደ ነው።

በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሥርዓቱን ለማዘመን እየሰራ ነው።

በዚሁ መሰረት ባለስልጣኑ በተለይም የኮሚዩኒኬሽን መሰረተ-ልማት አቅርቦትን ለማስፋትና በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያው የሚከናወነው በአገሪቱ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች በሚኖራቸው ደረጃ ላይ በመመስረት መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ ያሉት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎች ባለው የኔትወርክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚበለጽጉና የሚያድጉ ናቸው ብለዋል።

በዚህም መሰረት አሁን ላይ በአገሪቱ ያለው የኢንተርኔት መሰረተ-ልማት 4ኛው ትውልድ (4ጂ) መድረሱን ጠቁመው ይህም በአዲስ አበባ ተግባራዊ መሆኑን አቶ ባልቻ ጠቅሰዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋኑን ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አመልክተዋል።

አዳዲስ የቴሌኮም አቅራቢ ድርጅቶች ወደ አገር ይገባሉ ተብሎ ስለሚጠበቅም በቅርቡ 5ኛው ትውልድ (5ጂ) በኢትዮጵያ ይተዋወቃል ብለዋል።

ይህ የተለያዩ ሥራዎችንና አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ የታገዙ በማድረግ ፈጣንና የተቀላጠፈ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንደሚያመቻችም አክለዋል።

ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ ግብይትን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም