በትግራይ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል

52
መቀሌ ኢዜአ ህዳር 11/12 ዓ/ም--የትግራይ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ በአትሌቲክስ ስፖርት ክልላቸውና ሃገራቸውን የሚያስጠሩ ምርጥ ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ። አትሌቶችና የዘርፉ አሰልጣኞች በበኩላቸው በክልሉ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ አገራቸውን የሚያስጠሩ በርካታ አትሌቶች ማፍራት እንደሚቻል ተናግረዋል። በቢሮው የአትሌቲክስ ፌዴረሽን ፅህፈት ቤት ስራ አስፈጻሚ አቶ ገብረጊዮርግስ ጎይተኦም ለኢዜአ እንደገለፁት ''የአትሌቲክስ ስፖርት የጤና፤ የልማትና እድገት መሰረት ነው'' የሚል አመለካከት በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት በክልሉ ውስጥ በሚገኙ 52 ወረዳዎች የስፖርት ዘርፉን አንድ የልማት አካል አድርገው እንዲያዩት እየተሰራ ነው ብለዋል። በክልሉ ያሉ ወረዳዎች በአትሌቲክስ ስፖርት እንዲሳተፉ ሲጠየቁ አስቀድመው በጀት ስለማይዙ አብዛኛዎቹ ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ እንደነበር አቶ ገብረገርግስ አስታውሰዋል። ቀደም ሲል በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የግል ባለሃብቶችና አሰልጣኞች ተሳትፎ አጥጋቢ አልነበረም ያሉት ስራ አስፈጻሚው ስፖርቱን በፕሮጀክት ለማስፋት በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ አሰልጣኞች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል ። በማይጨው ከተማ የሚገኘው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከል አገርን ወክለው የሚወዳደሩ ምርጥ አትሌቶችን ለማፍራት በየዓመቱ ከትግራይና አፋር ክልሎች የተመለመሉ ከ45 በላይ ወጣቶችን እየተቀበለ በማሰልጠን ላይ መሆኑን ገልፀዋል ። በትግራይ ክልል የሚገኙ አትሌቶችና የዘርፉ አሰልጣኞች በበኩላቸው የክልሉ መንግስትና የግል ኩባንያዎች በቅንጅት ዘርፉን ለማጠናከር በሰሩት ስራ እነ ሐጎስ ገብረይህወት፣ለተሰንበት ግደይና ሌሎችን ሃገራቸውን ያስጠሩ ስመ ጥር አትሌቶችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል። ሆኖም ከዘርፉ ብዛትና ጥራት ያላቸው ታዳጊ ወጣቶችን ለማፍራት ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ዘርፉን በስፋት ቢሰራበት በርካታ ስመ ጥር አትሌቶችን ከክልሉ ማፍራት ይቻላል በማለት አስተያየቷን የሰጠችው በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ነዋሪ ታዳጊ አትሌት ማህደር መለሰ ናት። ማህደር እንደምትለው ወደፊት የስመ ጥሩዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ አርአያ በመከተል ክልሏዋና ሃገሯዋን ለማስጠራት ህልም እንዳላት ገልጻለች። ህልምዋን እውን ለማድረግም በትምህርትቤቶች መካከል ከሁለት ዓመት በፊት በ1ሺህ 500ና በ3 ሺህ ሜትር ርቀቶች በመሳተፍ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማግኘቷን ተናግራለች ። የአትሌቲክስ ስፖርት ይበልጥ ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና ሌሎች ተቋማት በእቅዳቸው ላይ በማካተት መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝ አቶ ተፈሪ ግደይ ናቸው። ከቤተሰቡ በሚደረግለት ድጋፍ በግሉ እየሰለጠነ በሦስት ሺህ ሜትር ሩጫ በመወዳደር  ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመውጣት ብቃቱን እያስመሰከረ የሚገኘው ወጣት ንጉሰ ታረቀ በበኩሉ የስልጠናና ሌሎች ድጋፎች ከተደረጉ በዘርፉ ብቁ ተወዳዳሪዎችን በብዛት ማፍራት ይቻላል የሚል ተስፋ እንዳለው ተናግሯል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም