የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባውን ጀመረ

193
ኢዜአ፤ህዳር 11/2012 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ዛሬ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል።
 

የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶችን በማዋሃድ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢሕአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ግንባሩን ከአጋሮቹ ጋር እንዲዋሃድና ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ እንዲሆን ሰሞኑን በአብላጫ ድምጽ መወሰኑ ይታወሳል።

ውህዱ ፓርቲ “ብልፅግና ፓርቲ” የሚለው ስያሜ ለኢሕአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከስምምነት መድረሱ መዘገቡም ይታወቃል። .

ሥራ አስፈጻሚው በሦስት ቀን ውሎው የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተመለከተ አማርኛን ጨምሮ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ለስራ ቋንቋነት የተመረጡ መሆኑንም አስታውቋል።

ፓርቲው በመተዳደርያ ደንቡ ላይ በአገሪቷ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱንም ገልጿል።

ብልፅግና ፓርቲ በፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር የሚሉትን ስያሜዎች የሚቀይር ይሆናል።