በምስራቅ ሸዋ ዞን የደረሰ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ ነው

63

አዳማ ኢዜአ ህዳር 10/2012፡- በምስራቅ ሸዋ ዞን የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ በኮምባይነር በመታገዝ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ የሰብል ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስሜ ብራቱ  ለኢዜአ እንደገለጹት በምስራቅ ሸዋ በ2011/2012 የምርት ዘመን  ከ437ሺህ በላይ  ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለምቷል።

ከዚህ ውስጥ  የደረሰ  325 ሺህ ሄክታር ላይ  የነበረ ሰብል መሰብሰብ ተችሏል።

የደረሰው ሰብል ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ   194 ኮምፓይነር ከባለሃብቶችና አቅራቢ ድርጅቶች በተመጣጣኝ ኪራይ በስድስት ወረዳዎች  ተሰማርተው  ለአርሶ አደሩ እገዛ እያደረጉ ናቸው።

በዚህም 46ሺህ ሄክታር የስንዴ አጨዳና ውቂያ በኮምፓይነር መከናወኑን የጠቀሱት ባለሙያው ጤፍና ሌሎች ሰብሎች አርሶ አደሩ በደቦና በቤተሰብ ትብብር እንዲያነሳ መደረጉን አስረድተዋል።

ባለሙያ እንዳሉት ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለይም በቦሰት፣ፋንታሌ፣አዳሚ ቱሉ፣ አዳማ፣ ዱግዳ፣ቦራ፣ሊበንና ሉሜ ወረዳዎች በዘመናዊ መሳሪያ ታግዘው የተዘራ የብርዕ ሰብል ከ90 በመቶ በላይ ተሰብስቧል።

በደጋማ የዞኑ አካባቢዎች በተለይም አደአና ጊንቢቹ ወረዳዎች የባቄላ ፣አተር ፣ሽንብራ ፣ምስርና ጓያ የመሳሰሉ የጥራ ጥሬ ሰብል  ወደ ኋላ የቀሩ ቢሆንም በተቀሩት ወረዳዎች የእስካሁኑ  አፈፃፀም  43 በመቶ ላይ መድረሱ ተመልክቷል።

“አምና በዋና ዋና ሰብል ከለማው መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት አግኝተናል” ያሉት አቶ ስሜ ዘንድሮ ደግሞ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከዞኑ አስተዳደርና ከሉሜ አዳማ ህብረት ሥራ ዩኒዬን ጋር በመተባበር  ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ አርሶ አደሩ የኮምፓይነር አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ 70 በመቶ የሚሆነው የስንዴ ማሳ መሰብሰቡን የተናጉት ደግሞ የሉሜ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ ደምሴ ናቸው።

በወረዳው ከጥራ ጥሬ ውጪ ስንዴ፣ጤፍና የአገዳ ሰብል  90 በመቶ አጨዳው ተጠናቆ ወደ ውቂያ መገባቱን አመልክተው “አርሶ አደሩ አጨዳውንና ውቅያውን ጎን ለጎን ማስኬድ እንዲችል እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል።

በዚሁ  ረዳ የሸራዲባንዲባ ቀበሌ አርሶ አደር መድኃኒት ታደስ በበኩላቸው ” የደረሰ ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በመሰብሰብ ላይ እንገኛለን “ብለዋል።

በኮምፓይነር ሶስት  ሄክታር መሬት ስንዴ ማሳጨዳቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ ስድስት ሄክታር የሚሆነውን ጤፍና ሽንብራን ደግሞ በደቦና በቀን ሠራተኞች ጭምር እያሰባሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።