የሕክምና ቡድኑ ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና መስጠት ጀመረ

127
ህዳር 10/2012 የእስራኤል የልብ ሕክምና ቡድን ዛሬ በኢትዮጵያ ለ30 ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና መስጠት ጀመረ። ቡድኑ በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ውስጥ ለሚገኙ 30 ህፃናት የልብ ቀዶ ሕክምናና ተያያዥ ሕክምናዎችን እየሰጠ ይገኛል። የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው "የሕፃናትን ልብ ማዳን" የሚል ተልዕኮ አንግቦ በሚሰራው የእስራኤል በጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት ነው። በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራሽ በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ የሕጻናት የልብ ቀዶ ሕክምናው ከኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ጋር በትብብር እየተሰጠ ነው። የእስራኤል የሕክምና ቡድን በኢትዮጵያ እየሰጠ ያለው የሕክምና አገልግሎት የመጀመሪያው ሲሆን "ሕጻናትን በመርዳት በኩል ከኢትዮጵያ ጋር አጋር መሆናችን ያስደስተናል" ብለዋል። እስራኤል በሕክምና ዘርፍ ለኢትዮጵያ በምታደርገው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደሩ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የአጋርነት ማረጋገጫ እንደሆነም ተናግረዋል። ሴቭ ኤ ቻይልድስ ኸርት የእስራኤል በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ተጠሪ ሲሞን ፊሸር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች በዘርፉ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ የሚገኙ ሲሆን በልብ ሕክምናና ቀዶ ሕክምና ላይ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ከእስራኤል የመጣው የልብ ህክምና ባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ለ30 ህጻናት የልብ ህክምና እንደሚሰጥም ገልጸዋል። ''ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአጋርነትና የመልካም ግንኙነት ውጤት ሲሆን ወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደርገዋል'' ብለዋል። ከቀዶ ሕክምና አገልግሎቱ ባሻገር ለሕፃናቱ የቅድመ ምርመራና ቀደም ሲል ሕክምና ያላደረጉ ክትትል የሚደረግ መሆኑ ገልጸዋል። የሕክምና ቡድኑ አገልግሎት ለኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል የሕክምና ቁሳቁስ ማሟላትን እንደሚጨምርም ተናግረዋል። የላቦራቶሪ፣ ዘመናዊ የቀዶ ሕክምና ክፍልና የጽኑ ሕክምና ክትትል ባለሙያዎች ስልጠና ማቅረብንም ያካትታል ብለዋል። በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፍቃዱ በበኩላቸው የሴቭ ኤ ቻይልድስ ኸርት የበጎ አድራጎት ድርጅት ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል። ባለሙያዎችን በማሰልጠንና አገር ውስጥ ቀዶ ሕክምና ሊሰራላቸው የማይችሉትን ወደ እስራኤል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ እያገዘ መሆኑንም ጠቁመዋል። "ማዕከሉ ከሁለት ዓመት በፊት ያሰለጠናቸው 12 ሐኪሞችና 60 የጤና ባለሙያዎች አሁኑ ወቅት ራሳቸውን ችለው ህክምና እየሰጡ ናቸው'' ብለዋል። "ሴቭ ኤ ቻይልድስ ኸርት" ከዚህ በፊት ለዘጠኝ ኢትዮጵያውያን የልብ ህክምና ስፔሻሊስቶች ስልጠና የሰጠ ሲሆን ዘጠኙም ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ማዕከሉ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ1995 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በ62 አገራት ለሚገኙ ሕፃናት የልብ ሕክምና እየሰጠ ይገኛል። የሕክምና ቡድኑም በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ 25 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን ከ700 በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የልብ ቀዶ ሕክምናና ተያያዥ ሕክምና ሰጥቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም