የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር የተቋማትና የአሰራር ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል

98
ኢዜአ ህዳር 10 ቀን/2012 በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር መንግሥት የተቋማትና የአሰራር ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ። በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሣምንት በአፍሪካ ኅብረት ለአምስት ቀናት የሚቆይ አውደ ርዕይና ምክክር እየተካሄደ ነው። ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በ2025 የማምረቻ እምብርት ለመሆን ውጥን አላት። ይህንንም ለማድረግ ተመጋጋቢ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን መንደፍና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የመፍጠር ሥራ መስራቷን ገልጸዋል። የኢንቨስትመንት መስኮችን የመለየትና የማምረቻ ዘርፉን ለማቀላጠፍ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። አሁን ደግሞ ከዚህ ቀደም ለኢንቨስትመንትና የማምረቻ ዘርፍ ልማት ለማስፋፋት የሚያዳግቱ አሰራሮችን የመፈተሽና የማሻሻል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከአነዚህም መከካል በቅርቡ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግ ከዚህ ቀደም ለግሉ ዘርፉ ክፍት ያልነበሩ ተቋማት ክፍት እንዲሆኑ ወስኗል ብለዋል። ሕጉ አገሪቷን በዓለም የኢንቨስትመንት ምህዋር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የኢንቨስትመንት አማራጮችንም እንዲታይ ረድቷል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ። በተለይም በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ መደረጉን ከማሻሻያዎቹ እንደ አንድ አዎንታዊ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል። ይህም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማቀላጠፍ የአገሪቱን የማምረቻ ዘርፍ ልማት ለማሳደግና ለማሰፋት ወሳኝ አርምጃ መሆኑን ነው የገለጹት። ጎን ለጎንም የውጭ ንግድን ለማሳለጥ የሚካሄዱት የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እምርታ እየታየባቸው መሆኑንና እንዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አክለዋል። በተለይም በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ የአሰራር ግድፈቶች እየታረሙ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ይህም ከዓለም አቀፍ ገበያው ጋር ለመተሳሰር ያስችላል ነው ያሉት። ያም ብቻ ሳይሆን በንግድ ዘርፍ የሚሳተፈው ተዋናይ እንዲበዛና ምጣኔ ኃብቱም ከአንድ ምርት ላይ ትኩረቱን እንዲያነሳ እንደሚጠቅም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በአግባቡ እንዲተገበር ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሌሎች የአፍሪካ አገራትንም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም