የህክምና ኮሌጁ 33 የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ

74
ኢዜአ ህዳር 10 / 2012 ዓ.ም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ኮሌጅ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር የሚረዱ 33 የምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የኮሌጁ ተባባሪ የአካዳሚክና ምርምር ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሴር መሃመድ ሱለይማን እንደገለፁት ኮሌጁ በበጀት ዓመቱ 23 አዳዲስ የምርምርና 10 የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የተመለከቱ ተግባራት እያከናወነ ነው ። ለስራዎቹ  ማስፈጸሚያም  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስረድተዋል፡፡ የምርምር ስራዎቹ በማህበረሰብ ጤና አገልግሎት አሰጣጥና ጉድሌቶች፤በመማር ማስተማር ሂደት፤በጤና አመራር፤ በአከባቢው ያሉ የጤና ተቋማት ቁመናና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው ብለዋል ። በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች ዘርፍም የወጣቶች ስነ-ተዋልዶ ጤና፤የማህጸን ጫፍ ካንሰር መከላከያ፤የከተማ ንጽህናና መሰል ጉዳዮች ትኩረት ከሚሰጣቸው አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ። ኮሌጁ ሆስፒታልም ጭምር የሚያስተዳደር በመሆኑ ከህዝብና ከመንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትና ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ራሱን እያዘመነ ለመሄድ የሚያስችለውን ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል ። ለምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የተሰጠው ትኩረት የኮሌጁን ዓለም አቀፍ ዕውቅና በመጨመርና የውጭ ግንኙነትን በማጠናከር  የቴክኖሎጂ መቅዳትን ጨምሮ ለሃገራዊ ክህሎት ግብአትነት እንዲውል የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል ። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር መስፍን ቢቢሶ በበኩላቸው በሆስፒታሉና በአካባቢው ባሉት የጤና ተቋማት ላይ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት ችግሮች ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ስራ እየተካሔደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ሆስፒታሉ አጎራባች ዞኖችን ጨምሮ በዓመት ከ5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህብረሰብ የሚያገለግል በመሆኑ በግብአትና በሰው ሃይል የተደራጀ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡ በኮሌጁ የሚድ ዋይፌሪ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ክብረአብ ጳውሎስ ከስድስት ዓመት በላይ በዩኒቨረሲቲው ማገልገላቸውን ገልጸው ምሁራንን በምርምር ለማብቃት የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኬሌጁ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ህዝቡ የሚቸግርባቸውን ተግባራት እየለየ ለመፍታት የሚያከናውናቸው ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ተመራማሪው ሃሳብ ሰጥተዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም