የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ሊያተኩር ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

51
ኢዜአ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ በትኩረት እንዲሰራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። ኮሚሽኑ ዛሬ የ2012 የሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል። በሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 700 ሚሊዮን ዶላር ማሳካት ችሏል። የኢንቨስትመንት ኮሚሺነር አበበ አበባው ባቀረቡት ሪፖርት አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ዕድገት እንዳለው ነው የገለጹት። በተያዘው በጀት ዓመት ዕቅድ ልክ እንዳይሰራ በአገሪቷ የተከሰተው የሠላም እጦትና አለመረጋጋት ምክንያት አንደሆነም አውስተዋል። ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የውጭ ቀጥተኛ ንግድ ገቢ ካለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም በተለይ የአዳማ፣ የመቀሌና የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዝቅተኛ አፈጻጸም ማሳየታቸውን ገልጿል። በመሆኑም ለፓርኮቹ የተሻለ ድጋፍ በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስቧል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ለፕሮጀክቶች የሚደረግ ድጋፍና ክትትልን በተመለከተ የሚገጥሟቸውን የመሰረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር መፍታት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከፓርኮች ውጪ እየተፈጠረ ያለው የስራ ዕድል አበረታች ቢሆንም ከዘርፉ ከሚጠበቀውና እንደ አገር ካለው የስራአጥ ቁጥር አንጻር በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ  አስገንዝበዋል። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ከባቢን ምቹ ከማድረግ፣ የኤክስፖርት ስራዎችን ከማሻሻል፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ከማስፋፋት አኳያም ሰፊ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል። ኮሚሽኑም በሩብ ዓመቱ 1 ሺህ 307 የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠት የምዝገባና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት አቅዶ ከ2 ሺህ 500 በላይ መፈፀሙን አስታውቋል። ለ23 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶም ከ24 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ በቀረበው ሪፖርት ተጠቅሷል። ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችና አቅጣጫዎችን በመከተል በቀጣይ በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም