የኢህአዴግ ምክር ቤት ነገ ይሰበሰባል

77
ህዳር 10/2012 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ስብሰባውን ያደርጋል። ግንባሩ ነገ ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም የምክር ቤቱን ስብሰባውን እንደሚያካሂድ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በቅርቡ ኢህአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ በአብላጫ ድምጽ ግንባሩን ከአጋሮቹ ጋር እንዲዋሃድና ሕብረ ብሔራዊ  ፓርቲ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል። ውህዱ ፓርቲ “ብልፅግና ፓርቲ” የሚለው ስያሜ ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከስምምነት ላይ መድረሱ መዘገቡ ይታወቃል። . ሥራ አስፈጻሚው በሦስት ቀን ውሎ የፓርቲው የስራ ቋንቋን በተመለከተም አማርኛን ጨምሮ አፋን ኦሮሞ፣ ሱማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች ለስራ ቋንቋነት የተመረጡ መሆኑም አስታውቋል። ፓርቲው በመተዳደርያ ደንቡ ላይ በአገሪቱ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱንም ገልጿል፡፡ ብልፅግና ፓርቲ በፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሊቀ-መንበር የሚሉትን ስያሜዎች የሚቀይር ይሆናል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ3ኛው ቀን ውሎው በፓርቲው ረቂቅ ህገ ደንብ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳቦቹ ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርቡ የወሰነ ሲሆን፤ የነገውም ስብሰባ የሥራ አስፈጻሚው ለምክር ቤቱ ያስተላለፋቸውን አጀንዳዎች ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይገመታል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም