የፓርቲው ውህደት ለህዝቦች አንድነት ጠንካራ መሰረት ይጥላል

53
ኢዜአ ህዳር 9/ 2012 ዓ.ም የኢህአዴግ ውህደት የብሄር፤ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነት በጠንካራ መሰረት ለማቆምና የፓርቲውን የመፎካከር አቅም የሚያጎለብት መሆኑን የድሬዳዋና የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ገለፁ ። የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የኢህአዴግ ውህደት አግላይ የነበረውን አሠራር በማስተካከል ትክክለኛውን የፌደራል ሥርዓት ለመገንባት ያግዛል ብለዋል ። የድሬዳዋ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበበ ታምራት እንደገለፁት የኢህአዴግ መዋሃድ ለይስሙላ ሲተገበር የነበረውን የፌደራሊዝምሥርዓት ወደ ትክክለኛው  ይለውጠዋል  ፡፡ እንደማሳያ የጠቀሱት አጋር ተብለው ሲጠሩ የነበሩት 5ቱ ድርጅቶች በሀገራቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የመሳተፍ፣ የመወሰንና ሀገር የመምራት እድል ጭምር የሚያጎናፅፋቸው በመሆኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ የሚደገፍ ነው ። በተጨማሪም ያላቸውን ተፈጥሯዊ ሃብት በተገቢው መንገድ በመጠቀም ለክልሎቻቸውና ለሀገር ምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛቸዋል ። ኢንጂነር ጀማል አቡበከር በበኩላቸው ውህደቱ ለ27 ዓመታት የአንድ የፖለቲካ ድርጅት የበላይነት የነገሰበትና አዳጊ ክልሎችን በሞግዚትነት እንዲተዳደሩ አድርጎ የቆየውን አሰራር የሚያስቀር ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን ገልፀዋል ። የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የኢህአደግ ውህደት የብሄር፤ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነት በጠንካራ መሰረት ለማቆም የሚረዳ ነው ብለዋል ። የወላይታ ዞን መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኤሊያስ ቦጋለ እንደገለፁት ኢህአደግ ተዋህዶ አንድ ብሄራዊ ፓርቲ ለመመስረት በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ መወሰኑ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል እየገነነ የመጣውን የመጠራጠር ስሜት በማስወገድ ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል ይላሉ፡፡ በብሄሮች መካከል የሰከነና ነባሩን ባህል ያከበረ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና አንድነቷ የተጠበቀች ሃገር ለመመስረት ውህደቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል ። ውህደቱ ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትና በጋራ የመልማት መርህን በአግባቡ ለመተግበር ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ከልብ እንደግፈዋለን ብለዋል ። ፅንፈኞች የየራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በአገሪቷ የተለያዩ ችግሮች በፈጠሩበት ወቅት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመዋሃድ መወሰኑ አቅሙን አሰባስቦ በቀጣይ የተረጋጋ ሠላም ለማስፈን እድል ይፈጥራል ያሉት ደግሞ በከተማው የሠላም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኢያሱ ወጋሶ ናቸው፡፡ የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መዋሀድ ለሰላም ፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ ፋይዳው የጎላ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት አቶ ኢያሱ ፓርቲው ሀገርን የማዳንና የህዝብ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ አደራውን በብቃት እንዲወጣ ያስችለዋል ብለዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም