ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ እንዲሰጡ መንግስት አስገዳጅ ህግ እንዲያወጣ ተጠየቀ

96
አዲስ አበባ ህዳር 10/2012 ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜ እንዲሰጡ መንግስት አስገዳጅ ህግ እንዲያወጣ ተጠየቀ። በአገር ግንባታ ሂደትም የወላጆች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ''የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል?'' በሚል ርዕስ ወርሃዊ ውይይት ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል። በመድረኩም ከተለያዩ ተቋማት የመጡ የስነ ልቦና ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። በዚሁ ጊዜ ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ''የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል ስንል ቀደም ሲል የተገነባ አገር የለንም ማለት አይደለም'' ብለዋል። ቀደም ሲል የተገነባን አገር ጠብቀን ማቆየት ሲገባን ወደ መከፋፈልና አገር ወደ ማፍረስ ድርጊት የመሄድ አዝማሚያዎች የታዩ መሆኑን በማንሳት። በተለይ ወጣቶች አባቶች ያቆዩትን አገር ጠብቆ የማቆየት ከፍተኛ ሃላፊትን እንዳለባቸው ገልጸው፤ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤትም ሆነ በስራ ቦታ ወጣቶችን የማነጽ ስራ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል። ወጣቶችን የማነጽ ሚና የመንግስት ብቻ መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል። ''የአገር ግንባታ መሰረቱ ቤተሰብ ነው'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ ልጆች መከባበር፣ መተጋገዝና ፍቅርን የሚማሩት ከቤተሰብ መሆኑን ገልጸዋል። ''ወላጆች በዕለት ተዕለት ስራም ይሆን በሌላ ጉዳይ ተጠምደው ከልጆቻቸው ጋር ውይይት ባለማድረጋቸው ለልጆች ባህሪ መቀየር አስተዋጽኦ አድርጓል'' ብለዋል። ከቤተሰብ ቀጥሎ የእምነት ተቋማት ብሎም ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሚና እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ወደፊት አገር የመረከብ ሃላፊነት ያለባቸው ልጆች እንዲታነጹ ለማድረግ ወላጆች ለልጆቻቸው በቂጊዜ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ህግ በመንግስት መውጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም