የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህዳሴ ግድብ ያለውን አቅም ለመጠቀም በትብብር እንዲሰሩ ተጠየቀ

74
ኢዜአ ህዳር 10/2012   የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር በማካሄድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዘርፈ ብዙ አቅም ለመጠቀም በትብብር እንዲሰሩ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አቀረበ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአሳ እርባታና ቱሪዝም መዳረሻ አንጻር ሰፊ ተጠቃሚነት የሚፈጥር መሆኑ ይታወቃል። የግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ሲኖረው፤ 13 ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 5 ሺህ 670 ጊጋዋት ሃይል እንዲያመርቱ ዕቅድ ተይዟል። በህዳሴ ግድብ የውሃ ማጠራቀሚያ ሰው ሰራሽ ሃይቅ በመስራት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ መኖሩም ይታወቃል። የግድቡ ሃይል ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉትና በተለይም ከአሳ ሀብት ልማት አኳያ እምቅ አቅም እንዳለው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚህም ረገድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዳሰሳ ጥናት ማድረግ አለባቸው ብለዋል። የአሳ እርባታው ላይ የሚያስፈልገው ጥናት ከተካሄደ በኋላ ወደ አሳ ምርቱ ሲገባ ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል። በተጨማሪም በአሳ ሀብት ልማቱ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። ከቱሪዝም አኳያም በአካባቢው ሰላምን የማረጋገጥ፣ ለቱሪስቶች ማረፊያ ማዘጋጀትና ለሚያገኙት አገልግሎት ተመጣጣኝ የሆነ የዋጋ ሊኖር ይገባል ብለዋል። በአጠቃላይ በህዳሴ ግድቡ አካባቢ ከወዲሁ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቅሰዋል። የአሳ እርባታና የቱሪዝም መዳረሻን ጨምሮ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለውን ለመጠቀም የተቀናጀ ፕሮጀክት መቅረጽና የህዳሴ ግድብ የልማት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ እንደሚገባውም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት። በዚህ ረገድ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአባይ ወንዝ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ህብረተሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወርቃማ ሀብቶቿን እንድትጠቀም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለው ተሳትፎ እምብዛም የሚባል እንደሆነና በቀጣይ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጠንክሮ እንደሚሰራ አክለዋል። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት መስጠት የጀመረው በ2010 ዓ.ም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም