ውህደቱ ልማትን ለማፋጠንና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ድርሻ አለው — አስተያየት ሰጪዎች

104

ኢዜአ  ህዳር 10 / 2ዐ12 የኢህአዴግ ውህደት ልማትን ለማፋጠን፣ ብቁ አስተዳደርን ለማስፈንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንዳንድ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኢ ህ አ ዴ ግ የውህደት ጉዞ ተመሳሳይ አቋምና  አላማ ያላቸው ድርጅቶች በአንድ ፓርቲ ስር መወሃዳቸው ለህዝብ የማያሻማ ምርጫና ለሀገር አንድነት የሚበጅ ተግባር ነው ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በፍቼ ከተማ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ጥበቡ እንደገለፁት የኢህአዴግ ውህደት የገጠር ልማትን ለማፋጠን፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ።

በተለይ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት የስልጣን ፣ የሀብትና የጥቅም ተካፋይ በማድረግ ለዘላቂ ሰላምና የእርስ በእርስ ግንኙነት በጎ አሻራ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የኢህአዴግ ውህደት ለዓመታት የፖለቲካ  ማደናገሪያና ማታለያ ሆኖ የቆየውን የአግላይነት ስርዓት እንዲያከትም እድል የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ማሞ በላቸው በበኩላቸው ውህደቱ የገጠርና የከተማ ልማትን ለማፋጠን፣ የህግ የበላይነትን ለማስፈን የቆመ ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር እድል የሚሰጥ በመሆኑ እንደግፈዋለን ብለዋል ።

በፍቼ ከተማ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ኑሪያ ኡስማን እንዳሉት  ደግሞ የፓርቲ ቁጥር ማብዛት ለተሸናፊነት የሚዳርግ ፣ የሀሳብና የተግባር አንድነትን የሚያፋልስ በመሆኑ ወደ ውህደትና አንድነት መምጣቱ የሚደገፍና የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል ።

በአሁኑ ወቅትም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ወደ ውህደት መምጣት ለሀገሪቱ ህዝቦች ሰላም ፣ ልማትና እድገት የሚበጅ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውህደቱ የሚፈጠረው ፓርቲም አባላቱና ደጋፊዎቹን አስተባብሮ ሁለንተናዊ  ለውጥ ለማምጣት ሰፊ እድል የሚሰጠው መሆኑን አውስተዋል ።

የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በላይ ወልደ ፃዲቅ በሰጡት አስተያየት የኢህአዴግ ውህደት አባልም ሆነ አጋር የሚባሉ  ድርጅቶች እኩል የሚሳተፉበትና የሚወከሉበት እድል በመፍጠር ለህዝብ እድገትና ብልፅግና የራሱ ድርሻ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

በተለይም ክልሎች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት  እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፣ ቋንቋና ባህላቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ አማራጭ የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢህአዴግ የውህደት ጉዞ ለሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥሩ አርአያ ነው ያሉት አባገዳ ዘነበ ቱፋ በበኩላቸው ሕዝቡም ከመበታተን ወደ አንድ በመምጣት ውህደትና አንድነት የጥንካሬ ምንጭ መሆኑን ሊማርበት ይገባል ብለዋል።