በአፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ቅጥር ጊቢ የሚገኙ ቅርሶች የአደጋ ስጋት ተጋርጦባቸዋል

116

ኢዜአ፤ ህዳር 10/2012 በአጼ ፋሲል አብያተ መንግስታት ቅጥር ጊቢ የሚገኙ ኪነ ህንጻዎች ዙርያ እየጨመረ በመጣው የተሸከርካሪዎች ፍሰት ቅርሶቹ ለጉዳት መጋለጣቸውን የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ በቅርሱ አካባቢ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ለመቀነስ ተለዋጭ መንገድ ለማመቻቸት የከተማውን መዋቅራዊ ፕላን የማሻሻል ጥናት ማከናወኑን አስታውቋል፡፡

የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ለኢዜአ እንደተናገሩት አለም አቀፋዊ ቅርሱ በሚገኝበት አራቱም አቅጣጫዎች ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች ያለገደብ የሚመላለሱበት ነው።

በከተማዋ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በተለይ በምእራብና በደቡብ አቅጫዎች በሚገኘው የአጼ በካፋ ህንጻ ላይ የመሰንጠቅና የማዝመም አደጋ ገጥሞታል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቅርሱ በብረት ተደግፎ እንደሚገኝ ና በተለይ ከባድ ተሸከርካሪዎች በሚፈጥሩት ከፍተኛ ንዝረት፤ የጭስ ብክለትና አልፎ አልፎም በጊቢው አጥር ላይ የሚከሰት ግጭት ስጋቱን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡

በስተደቡብና በምእራብ አቅጣጫዎች ከፒያሳ የሚነሳው ዋና መንገድ በአፋጣኝ ተለዋጭ መንገድ ተገንብቶ መንገዱን ከተሸከርካሪ ምልልስ ነጻ ማድረግ ካልተቻለ በቅርሱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማስቀረት አዳጋች ይሆናል ብለዋል፡፡

መምሪያው በቅርሱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ስጋት ለከተማ አስተዳዳሩ በተደጋጋሚ ማሳወቁንና በከተማው ምክር ቤት ጉባኤ ጭምር በመገኘት የችግሩን አሳሳቢነት ለማስገንዘብ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የከተማው አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳው በበኩላቸው ቅርሱን ከአደጋ ስጋት ለማላቀቅ በቅርቡ ለከተማው ምክር ቤት የተለዋጭ መንገድ መዋቅራዊ ፕላን ማሻሻያ ጥናት ቀርቦ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

በመዋቅራዊ ፕላን ማሻሻያውም ከሰርክል ሆቴል እስከ አቦ ቤተ-ክርስቲያን የሚወስደውን መንገድ ተለዋጭ መንገድ ሆኖ እንዲያገለግል የመንገዱ ዲዛይን ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ተለዋጭ መንገዱ ስፋቱ 24 ሜትር እንዲሆን የቀረበው ሃሳብ በርካታ ቤቶችን የሚያፈርስና የካሳ ክፍያው በከተማ አስተዳዳሩ ላይ የበጀት ጫና የሚፈጥር በመሆኑ በአዲሱ ጥናት ስፋቱ ወደ 18 ሜትር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

የመንገዱ ዲዛይንና የወሰን ማስከበር ስራው እንደተጠናቀቀ ከተማ አስተዳደሩ በሚመድበው በጀት ግንባታውን ለማስጀመር መታቀዱንም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የከተማው ነዋሪዎች በበኩላቸው ተለዋጭ መንገዱ በቅርሱ ላይ ያጋጠመውን የመፍረስ አደጋ የሚታደግ በመሆኑ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም