የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጠት ተጀመረ

88
ኢዜአ ህዳር 10/2012 የሲዳማ ዞን በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ነው። በሃዋሳ ከተማ ምርጫ ጣቢያዎች የኢዜአ ሪፖርተሮች ተዘዋውረው እንደተመለከቱት ህዝቡ ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በየድምጽ መስጫ ጣቢዎያዎቹ ተሰልፏል። ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ሲሆንም ድምጽ መስጠት ጀምሯል። ከሃዋሳ ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቱላ የገጠር ከተማም ህዝቡ ከማለዳው ጀምሮ ድምጽ እየሰጠ ይገኛል። የድምጽ አሰጣጡ ሂደትም ሰላማዊ መሆኑን ሪፖርተሮቹ ተመልክተዋል። ለሲዳማ በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል። የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አሰጣጥ ለመታዘብ በሃዋሳ ከ300 በላይ የምርጫ ታዛቢዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በድምጽ መስጫው ዕለት ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ውሳኔ መተላለፉ አይዘነጋም። በዚሁ መሰረት ዛሬ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዝግ ናቸው። ገበያዎችና የጫት ግብይት በሚካሄድባቸው ሥፍራዎች በዕለቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይኖር ቀደም ብሎ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም