የኢህአዴግ ውህደት ለኢትዮጵያ የመካከለኝነት አማራጭ ያመጣል - ምክትል ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን

156
ኢዜአ ህዳር 9/2012  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህደት በዋልታ ረገጥ እሳቤዎች ለተወጠረችው ኢትዮጵያ የመካከለኝነት አማራጭ መፍትሄ እንደሚያመጣ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ። ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን ፣የቡድንና የግል መብቶችን አስጠብቆ መሄድም የውህደቱ መሰረታዊ ምሶሶዎች መሆናቸውን አክለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የኢህአዴግን ውህደት አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የፓርቲ ውህደቱን በሚመለከት የተደረገው ጥናት ግንባሩ የተጀመረውን ለውጥ በሚፈለገው ልክ መምራት በማያስችል መዋቅር ችግር ውስጥ መሆኑን አመላክቷል። ይኸው ችግር ኢትዮጵያን በብሄርና በሀገራዊ ማንነት በሚሉ ሁለት ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች እንድትወጠር ማድረጉን  ነው የተናገሩት። ''ውህድ ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትንና ብዝሃነትን እንዲሁም የግልና የቡድን መብቶችን ባከበረ መልኩ  የመካካለኛ አማራጭ መፍትሄ  ይዞ ቀርቧል'' ብለዋል። ይህን እውን ለማድረግ ውህደቱ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም፤ ብዝሃነት እንዲሁም የብሄርና የዜግነት መብቶችን ማክበርን ቁልፍ ምሶሶዎቹ አድርጎ መያዙን ጨምረው ገልጸዋል። ነገር ግን ውህደቱ ወደ አሃዳዊ ስርዓት ለመመለስ የሚደረግ ጥረትና የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚጨፈልቅ  አካሄድ አድርገው የሚተርኩ አካላት እንዳሉ ተናግረዋል። "ሀገርን ያህል ነገር ለመምራት የቆመ ፓርቲ እንዴት እንደዚህ አይነት ድብብቆሽ ውስጥ ይገባል?" ሲሉም የተነሳውን ሃሳብ በጥያቄ ሞግተዋል። ፓርቲው የቀጣይ ፕሮግራሞችና አወቃቀር በግልጽ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው፤ ውህደቱ ድርጅቱ የገጠመውን ችግር ፈቶና ህብረብሔራዊነትን ጠብቆ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር እንጂ ሌላ ምንም የተደበቀ ዓላማ እንደሌለውም አውስተዋል። ውህደቱን በሚመለከት  በልዩነት የወጡ የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ ልዩነት መጣላት ሳይሆን የዴሞክራሲ ስርዓት አንዱ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል። በልዩነት ውስጥ ገዢ የሆነውንና ብዙሃኑ የወሰኑትን ሃሳብ መቀበል እንደሚገባ በመግለጽ። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በድርጅቱ ውህደት፣ በአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራምና በህገ ደንብ ዙሪያ መወያየቱ ይታወቃል። በውይይቱም ስራ አስፈጻሚው በሶስቱም አጀንዳዎች ላይ የሚያግባባና የሚያቀራርብ ሃሳብ ማንጸባረቁን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም