አጎራባች ክልሎችን የሰላምና የልማት ቀጠና ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ይገባል...የፌዴሬሽን አፈ ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
አጎራባች ክልሎችን የሰላምና የልማት ቀጠና ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ይገባል...የፌዴሬሽን አፈ ጉባኤ
አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2012 የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎችን የሰላምና የልማት ቀጠና ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ።
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በመድረኩ ላይ እንዳሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሰላም እጦት ሲከሰት ይስተዋላል።
" በእዚህም ዜጎች በሰላም ተንቀሳቅሰው የመስራትና ሀብት የማፍራት መብታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል" ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ዋስትና አጥተው በጉልበተኞች ጉዳት የሚደርስባቸውና ለሞት የሚዳረጉበት ሁኔታ የተስተዋሉባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
"ሰላምን እያደፈረሱ ያሉት ጥቂት አካላት ናቸው" ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታና ልማትን ለማፋጠን የአገሪቱ ህዝቦች የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበር፣ የመተጋገዝና የመዋደድ እሴቶችን ማጠናከርና ለመጪው ትውልድ ማውረስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"ለዘመናት የዳበሩ እነዚህ እሴቶች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው በህብረተሰቡ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጉዳት ሳያስከትሉ የማይፈቱበት ሁኔታ ተስተውሏል" ብለዋል።
ሁሉም አካላት ቁርጠኛ ከሆኑ አገሪቱን ወደሰላምና መረጋጋት መመለስ እንደሚቻል የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ ፣ መድረኩም በጋራ ችግሮች ላይ በመወያየት በህዝቦች መካከል ያለው ሰላማዊ ግንኙነት እንዲጠናከር የማድረግ ዓላማ እንዳለው አስታውቀዋል።
አፈጉባኤዋ እንዳሉት የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎችን የሰላምና የልማት ቀጠና ለማድረግ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር ያስፈልጋል።
የአጎራባች ክልሎች ህዝቦች ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋና እምነት ያላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ እርሻና ግጦሽ አንድ ላይ የሚጠቀሙ ወንድማማች በመሆናቸው ይህንን አኩሪ እሴት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እያጋጠመ ያለውን ችግር ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲካ መሪዎች፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከሁሉም አካላት ጋር በጋራ በመምከር መፍታት እንደሚቻልም ወይዘሮ ኬሪያ አመልክተዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው መጠኑ ቢለያየም የህዝቦችን በሰላም አብሮ የመኖር ህልውናና እሴት የሚፈታተኑ ሰው ሰራሽ ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲከሰቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የጸጥታ ችግር እንዲኖር የሚያቀነባብሩት ለውጡን ማደናቀፍ የሚፈልጉ ጥገኛ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸው አገራዊ ለውጡ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሎሚ እንዳሉት ህዝቡ የለውጡን ፍሬዎች በመንከባከብ ከማንኛውም አደናቃፊ ኃይል ለመጠበቅ ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል።
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ የሚከበረው “ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ማከነ-ኢየሱስ ዋና ጽህፈት ቤት ተባባሪ ጠቅላይ ፀሐፊ ፍቃዱ ቤኛ በበኩላቸው የብሔር በሔረሰቦች በዓል በአገሪቱ የሚገኙ ህዝቦች አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና እርስ በርስ ባህላቸውን የሚለዋወጡበት መሆኑን ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ ሁሉንም ወገን በማቀራረብና በማፋቀር ወደ አንድ አገራዊ ግንባታ የሚያስኬድ እንደሆነም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ስርዓት ነባራዊ ሁኔታ፣ ስጋቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡ ምሁር ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።