የአፍሪካ ህብረት ደቡብ ሱዳን በአፋጣኝ መንግሥት እንድትመሰርት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

90
ኢዜአ  ህዳር 9/2012 የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽን ኮሚሽነር ስማኤል ቼጉሪ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ልዩነቶቻቸውን በመፍታት የአንድነት ብሔራዊ መንግሥት ለመመስረት የመጨረሻ ዕድል መሰጠታቸውን ተነግሯል፡፡ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና በቀድሞ ምክትላቸው  ሪክ ማቻር የሚመራው የተቃውሚ ሃይል ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት በርካታ ወራት የፈጀ ውይይት ካደረጉ እና አሜሪካም በበኩሏ በሁለቱም ወገን ላይ አስተማሪ ነው ያለችውን እርምጃ ለመውሰድ ማስጠንቀቋን ተከትሎ ነው ህብረቱ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ብሏል ዘገባው፡፡ ሱዳን ትሪዩቡን የኮሚሽነር ቼጉሪን በዋሽንግተን ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት ጠቅሶ እንደዘገበውም ለህዝባቸው ፈቃድ ምላሽ ለመስጠት ይህ ምናልባትም የመጨረሻ ዕድላቸው ይሆናል ብለዋል፡፡ ዋሽንግተን በደቡብ ሱዳን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደስተኛ አለመሆኗን የገለፁት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ቲቦር ናጅ  የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት ብሔራዊ  የአንድነት እና የሽግግር መንግሥት የማይመሠርቱ ከሆነ አሜሪካ ሌላ ይሆናል ያለችውን አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማትልም ገልፀዋል፡፡ በዋሽንግተን የተካሄደው ውይይት ሁለቱም የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይላት የብሔራዊ የአንድነት የሽግግር  መንግሥት ምሥረታውን ለተጨማሪ 100 ቀናት እንዲራዘም ከወሰኑ በኋላ መሆኑንም  አይ ኦ ኤል የተሰኘው ድረ-ገፅ በመረጃው ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም