በከተማ ግብርና ዘርፍ ግልጽ አሰራርና ስትራቴጂ ባለመኖሩ ውጤት አልተመዘገበም ተባለ

1566

አዳማ ሰኔ 13/2010 በከተማ ግብርና ዘርፍ ግልጽ አሰራርና ስትራቴጂ ባለመኖሩ ውጤት እየተመዘገበ አይደለም ብሏል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር።

ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት አዲስ ስትራቴጂ ረቂቅ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በስትራቴጂው ላይ ቁልፍ ችግሮችን በመለየት ውይይት ካደረገ በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በማጸደቅ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁሟል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዚር ገብረእግዚአብሔር እንደተናገሩት በአገሪቱ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግብርናው ዘርፍ የላቀ ሚና አለው።

ለዚህ የድህነት ማሸነፊያ ስልት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ የከተማ ግብርና አንዱ ተደርጎ ሲሰራ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የከተማ ግብርና ልማት ስትራቴጂና ኤክስቴንሽን ስርዓት አለመኖር፣ ወጥ የሆነ አደረጃጀት አለመዘርጋት፣ ስለ ከተማ ግብርና ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ያለው የግብዓትና አቅርቦት ጥራት ችግር ዘርፉ እንዳይስፋፋ ማነቆ ሆነው ከቆዩ ችግሮች መካከል ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሮቹን በማስወገድ ዘርፉን ለማሳደግ አዲስ ረቂቅ ስትራቴጂ ተቀርጾ ውይይት ተደርጎበት ከጸደቀ በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ሌሎች የልማት ስትራቴጂዎች በከተሞች ያለውን የግብርና ልማት አቅም ለማሳደግ የከተማ ግብርና ስትራቴጂ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በመንግስት ለማጸደግ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌዴራል ከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የኢንተርፕራይዞች ልማት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ባላ የከተማ ግብርና ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘርፍ ቢሆንም ግልጽ የሆነ አሰራርና ስትራቴጂ ባለመኖሩ ጥቅም እየተገኘበት አይደለም ብለዋል።

የስትራቴጂው መዘጋጀት በዘርፉ ተግዳሮት ሆነው ለቆዩት የማልሚያ መሬትና የብድር አቅርቦት ለመሳሰሉት ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ከተሞችም ለግብርና ልማት ስራ የሚውል ቦታዎችንና ሌሎች የግብዓት አቅርቦቶች የማዘጋጀት ስራ በዕቅዳቸው አካተው እንዲሰሩ በረቂቁ በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል።

የከተማ ግብርና በከተማና ዙሪያ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በምርትና ግብዓት አቅርቦት በማስተሳሰር የምግብ ፍላጎትን በማሟላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የከተማ ግብርናን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ በውል በመረዳት የዘርፉን የመልማት አቅም በመጠቀም ችግሮችን ለይቶ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ አሰራሩን ማሻሻል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግም አጋር አካላት በከተሞች አካባቢ የከተማ ግብርና አስፈላጊነትን በሚመለከት የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ጸድቆ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ መንግስት አስፈጻሚ አካል እንደሚያቋቁም አቶ በለጠ ጠቁመዋል።