ለአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጥ እንደሚሰሩ በሐረሪ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

89
ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም---ከማህበረሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ። በክልሉ በሚገኙ ዘጠኙም ወረዳዎች በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን እንደተናገሩት፣ የሃይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ወጣቶች ሰላም እንዲሰፍን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል። "ወላጆች ልጆቻቸውን በመምከር፣ የሃይማኖት አባቶችም ስለ-ሰላም በመስበክ፣ ወጣቱም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ የፀጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ መስራት ይገባናል" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት እየተፈጸሙ ያሉ ያልተገቡ ድርጊቶች በስልምና ሃይማኖት ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጹት ሼህ መሀመድ "ድርጊቱ የኢትዮጵያዊያንን እሴትም አይደለም" ብለዋል። ሁሉም ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ሰላምን ማስፈን እንዳለበት ጠቁመው እርስ በርስ በመደጋገፍ አብሮ የመኖር እሴትን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል። አንዳንድ የአመራር አካላት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲጋጭ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዲኖ ኢብራሂም ነው። "ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው በመስራት እነኚህን አካላት መከላከል ይኖርባቸዋል" ያለው ወጣቱ፣ የጥፋት ኃይሎች በወጣቱ ግባቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት ለመከላከል እንደሚሰራ አስታውቋል። ከማህበረሰቡና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ በመስራትም የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግሯል። አቶ መፍቱ መሀመድ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ በበኩላቸው ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። የአካባቢው ሰላም እየታወከ ያለው ከሌሎች አካባቢዎች በሚመጡ ቡድኖች መሆኑን ጠቁመው የክልሉን ሰላም ለማስፈን እጅ ለእጅ ተያይዞ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተዋል። "በተለይ ወጣቱ በተለያዩ የብዙሀን መገናኛዎች የሚለቀቁ የሃሰት መረጃዎችን ማጤን ይኖርበታል" ሲሉም ተናግረዋል። “በመንግስት አካላት የሚታዩ ክፍተቶች መታረም አለባቸው” ሲል የተናገረው ወጣት ኤልያስ ኢብራሂም በበኩሉ በተለይ የፓሊስ አባላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቋል። "በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል ማድረግ ያለበትን ትቶ ፖለቲከኛ እየሆነ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ብቻ ቢያተኩር መሰል ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ይቻላል" ብሏል። በመድረኩ ላይ ከደቡብ ምስራቅ ዕዝ የተገኙት ኮሎኔል ንጋቱ አዱኛ እንዳሉት ችግሮችን ከኃይል ይልቅ  በውይይትና በመረዳዳት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት። ህብረተሰቡ የአካባቢው ሰላም እንዲያጠናከር በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ገልጸው በተለይ ወጣቱ ለውጡን ለማደናቀፍ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል። "ወጣቱ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር እንዲጋጭ ጥረቶች ቢደረጉም አልተሳካም" ያሉት ኮሎኔሉ፣ ህብረተሰቡ በብሔር እና በሃይማኖት ተከፋፍሎ እንዲጋጭ የሚያደርጉ አካላትን ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መከላከል አንዳለበት አመልክተዋል። በውይይቱም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም