ወጣቶች ከማህበራዊ ሚዲያ በሚገኙ መረጃዎች ብቻ ታጥረዋል

1202

ህዳር ወቅታዊና ፈጣን መረጃ የሚሰጥ ሚዲያ በብዛት ባለመኖሩ ከማህበራዊ ሚዲያ በሚገኙ መረጃዎች መታጠራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ በፌስ ቡክ ላይ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው ታዋቂ ሰዎች በበኩላቸው መረጃን ለማጣራት በሚደረገው ጥረት የመንግስት ሃላፊዎች ትብብር አናሳ ነው አሉ።

አገሪቷ በተለያዩ ጊዜያት በሚለቀቁ የተሳሳቱ፣ የተጋነኑ እንዲሁም ሚዛናቸውን ባልጠበቁ መረጃዎች ሳቢያ ከፍተኛ ቀውስ እያስተናገደች ነው።

ለዚህም ማህበረሰቡና መንግስት ተጠያቂ እያደረገ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አውድና የዘርፉ ተዋናዮችን ነው።

የማህበራዊ ሚዲያ ዋነኛ ተጠቃሚና ተጠቂ ደግሞ ወጣቶች ናቸው።

ይኸን ያስተዋለው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ደግሞ እውነትም ማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖው ጉልህ መሆኑን ይናገራሉ።

ወጣት ይሁነኝ ማህመድ እንደሚለው በማህበራዊ ድህረ -ገጽ እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በፍጥነት የማግኘት እድሉ ሰፊ እየሆነ መጥቷል።

ትክክለኛ መረጃ ይሰጣሉ ተብለው የሚታመኑ የመንግስትም ይሁን የግለሰብ መረጃ ሰጪዎች በወቅቱ የመረጃዎችን “እውነተኛነትና ሃሰተኛነት ስለማያረጋግጡ የቀደመውን መረጃ ይዞ የመሄድ አዝማሚያ ይታያል” ብሏል።

በተለይ የመንግስት ሚዲያዎች በማህበራዊ ሚዲያ የተገለጹ ጉዳዮችን በዝርዝር የሚያቀርቡት ከሁለት ቀናት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ቀናት በኃላ በመሆኑ መንግስት ጉዳዩን ሊያስብበት ይገባልም ብሏል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ንጉሴ አድነው በበኩሉ ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም የራስን እውቀት ከማሳደግ ባለፈ ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት ይጠቅማል።

በተለይም ማህበራዊ ድረ-ገጽን  ለዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች፣  ለአዝናኛ ነገሮች፣ ለስነ ጽሁፋዊ ሀሳቦች ወዘተ ከፍተኛ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም አጠቃቀሙ ላይ ግን ክፍተት በመኖሩ “ለአገር አንድነት ስጋት አጭሯል” ይላል።

የማህበራዊ ድረ-ገጽ አጠቃቀም በተለይም “ፌስ ቡክ  ህግና ደንብ ሊበጅለት ይገባል”፤  እንዲሁም የጥላቻ ንግግር የሚያስተላልፉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገባው ጊዜ መዘግየት የለበትም ብሏል።

በተጨማሪም መንግስትም ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለሚወጡ ሚዲያዎችና ግለሰቦች እውቅና በመስጠት ትክክለኛ መረጃ የሚያስተላልፉትን ማብዛት አለበት ብለዋል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ በበኩሉ በርካታ የፌስ ቡክ ተከታይ ቢኖረውም መረጃዎችን በወቅቱ አጥርቶ ለህዝቡ ለማቅረብ የመንግስት ሃላፊዎች መረጃን የመስጠት ክፍተት አለባቸው ብሏል።

ስለዚህም ወጣቱ የመረጃ ጥማቱን ለማርካት ሲል የተሳሳቱ መረጃዎች ሰላባ ይሆናል ብሏል።

የመንግስት ሃላፊዎችም ሃሰተኛ ሚዲያዎችን እየተከታተሉ የማሳወቅና የማስተማር ሃላፊነታቸውን የመወጣት ተግባራቸው ዝቅተኛ ነው ብሏል ጋዜጠኛው።

ከቀደሙ ጊዜያት በላይ በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ሃላፊዎች መረጃ የማግኘቱ ችግር ተባብሶ ቀጥሏልም ነው ያለው።

በተለይም የመንግስት ሚዲያዎች የራሳቸውን ክልል ብቻ ለይተው የመዘገብ ነገር ይታያል ያለው ጋዜጠኛ ኤልያስ፤ “ይህ ደግሞ አገርና ወጣቱን አያንጽም” ብሏል ።

መንግስትም የህዝቡን መረጃ የማግኘት ነጻነት ለማረጋገጥ “መዋቅራዊ አሰራሩን ማሻሻል አለበት” ብሏል።

ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን በበኩሉ ሃሰተኛ መረጃዎችን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት “የመንግስት ሃላፊዎች ተባባሪ አይደሉም”።

በዚህም ምክንያት ምንጫቸው ባልታወቁ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ማህበራዊ ግንኙነትና የእርስ በእርስ ተግባቦትና ጠንካራ የሆነ ትስስር እያጠፋ ነው ብሏል።

ጋዜጠኛውም መረጃን በፍጥነት በጥራትና በትጋት በመስራት የወጣቱን የመረጃ ፍላጎት ያለመታከት መስራት አለበት ብለዋል።

ወጣቱም መረጃዎችን መርምሮና አገናዝቦ የመጠቀም ልምዱ መዳበር አለበት ብለዋል።