በአርሲ ዞን 83ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ርብርብ እየተደረገ ነው

82
ኢዜአ/ ህዳር 09/2012 በአርሲ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት 83 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ በመስኖ ለማልማት 32 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ። የአርሲ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሩን ከተፈጥሮ ዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅና  ገበያ ተኮር ምርቶችን በመስኖ ለማልማት የግንዛቤ ማስጨበጥና አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልጠዋል። በዘንድሮ ዓመት በዞኑ ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ልማት ለመሸፈን ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም  ተናግረዋል። ለእቅዱ ስኬታማነት እርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ዘንድ ያለውን የአቅምና የክህሎት ውስንነተ፣የአመለካከትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ለመሙላት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። ከዞን ጀምሮ የወረዳና የቀበሌ ገበሬ ማህበር የልማት ጠቢያ ሠራተኞችና ሙያተኞችን  ጨምሮ በግብዓት አጠቃቀም ፣በማስፈፀም አቅም ውስንነት፣የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማሳ ዝግጅት ላይ ሙሉ የኤክስቴሽን አገልግሎት ድጋፍ እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አቶ አባቡ አመልክተዋል። በተለይም የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮች የማፅዳት፣የውሃ መሳቢያ ሞተሮች የመጠገንና ለሥራ ዝግጁ የማድረግ፣ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ እያደረግን ነው ብለዋል። በሽንኩርት፣ቲማቲም፣ቃሪያ፣ድንች፣ጎመን፣ካሮትና ሌሎች የአትክልትና ስራስር ሰብሎችን ጨምሮ በቆሎና ስንዴ በመስኖ ለማልማት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በምግብ ራሱን እንዲችል ከማድረግ ባለፈ ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግና ኑሮው ከመሰረቱ እንዲለወጥ ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ብለዋል። እስከ አሁን ድረስ ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና የተለያዩ ምርጥ ዘሮች አርሶ አደሩ ዘንድ መድረሱን የተናገሩት አቶ አባቡ ዋቆ የተቀረውን 35ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 179 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ በህብረት ሥራ ዩኒዬኖች በኩል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ። በመስኖ ልማቱ 113 ሺህ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን በዞኑ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር ከ32 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጠዋል። አስተያየት ከሰጡት የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል የጀጁ ወረዳ ጉታ ጉሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ድንቁ አሰፋ እንደገለጹት በበጋ ወቅት በመስኖ በምናመርተው ሰብል ጥሩ ገቢ እያገኘን በመሆኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ2 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጁ ነኝ ብለዋል ። ማሳቸውን በተለያዩ አትክልቶች በተለይም ፎሶሊያ፣ሽንኩርት፣ቲማቲም፣ቃሪያና ቦቆሎ ለመሸፈን እየሰሩ መሆኑን አርሶ አደር ድንቁ ተናግረዋል። አምና ሽንኩርቲ፣ቲማቲምና በቆሎ በማምረት ከ250 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው ያለሙት የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአካባቢው አርሶ አደሮች ለዘር ማስረከባቸውን ገልፀዋል። በዞኑ የመርቲ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር የሽህ ደጉ በበኩላቸው በዘንድሮ ዓመት ሽንኩርት፣ቲማቲምና በቆሎን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን በ5 ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል ። እስከ አሁን ድረስ የሽንኩርቲና የቲማቲም ምርጥ ዘር በራሳቸው ማሳ ላይ ማባዛታቸውን  ጠቅሰው የበቆሎ ምርጥ ዘር ደግሞ ከአዋሽ ዩኒዬን መረከባቸውን ገልፀዋል። የወረዳ የግብርና ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በኤክስቴሽን አገልግሎትና ጠቀሜታ ላይ ስልጠና እየሰጡን ይገኛሉ ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አትክልትና ፍራፍሬ በተባይ እንዳይጎዳ የኬሚካል ግብዓቶች በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም