”የዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት – ለስጋና ወተት እድገት”

195

በምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በአብዛኛው በተፈጥሮ ደን የተሸፈነና ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞችና ጅረቶች በብዛት የሚገኙበት አካባቢ ነው::

ይህንኑ የተፈጥሮ ሀብት ተከትሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆኑ የተፈጥሮ ቡና : ማርና የቅመማ ቅመም ሰብሎች በቀላሉ ማልማት ይቻላል ።

ይኽው በተፈጥሮ ይዘቱ የታደለ አካባቢ እንደ ሀብት መጠኑ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ተገቢውን አስተዋፅኦ እያበረከተ አለመሆኑ ደግሞ ቁጭት ማስከተሉ አልቀረም ።

በተለይ ከላይ ከተጠቀሱት እምቅ ሀብቶቹ በተጨማሪ የእንስሳት መኖ ክረምት ከበጋ እንደ ልብ የሚገኝበትና የአየር ንብረቱም ለእንስሳት እርባታ አመቺ መሆኑ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ መጥቷል ።

እምቅ ሀብቱን ታሳቢ በማድረግም በቅርቡ አራት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የአካባቢውን አመቺነት በመጠቀም የእንስሳት ልማት ፕሮጀክት በጋራ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል::

በመቱ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀው መድረክ ስምምነቱን የተፈራረሙት የመቱ: ወለጋ: አምቦና ጅማ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው::

በዚሁ ጊዜ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ጌታቸው ተረፈ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በአራቱ ዩኒቨርስቲዎች የጋራ ተሳትፎና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ደጋፍ የሚከናወን ነው::

ፕሮጄክቱ በዋናነት የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ ለቀጣዮቹ አስር አመታት የሚከናወን ነው::

ዋና ዋና ተግባራቱም የአካባቢውን ነባር የቀንድ ከብት ዝርያ በተሻሻሉት መተካት ፣የእንስሳት እርባታ ፣ የመኖ ልማትና የስጋና ወተት ምርት ማቀነባበርያ ፋብሪካ ማቋቋም እንደሆነ አስተባባሪው ይናገራሉ።

የአካባቢውን አርሶአደሮችና ወጣቶች በባለቤትነት በማሳተፍ የስራ ዕድል መፍጠርና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው ተብሏል ።

የልማት ፕሮጄክቱን በዚህ አመት በኢሉአባቦር ቡኖ በደሌና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለመጀመር ሰባት የእንስሳት ልማት ጣቢያዎች ተቋቁመዋል::

ዶክተር ጌታቸው እንዳብራሩት በዚህ የእንስሳት ልማት ፕሮጀክት በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ከ370 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶችን በማዳቀል ዝርያቸውን ለማሰሻሻል ታቅዷል ።

ይህም በአሁኑ ወቅት ከአንድ ላም የሚገኘውን 2 ሊትር ወተት ወደ 12 ሊትር ለማሳደግ ያስችላል::በልማት ፕሮጀክቱ ንድፍ መሰረት አርሶአደሮችና ወጣቶች በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ።

አርሶ አደሩ እንስሳቱን በተሻሻለ ዝርያ ካዳቀለ በኋላ ለእርባታ ጣቢያው በማስረከብ ከሚገኘው የስጋና ወተት ምርት እንደ አስተዋፅኦው መጠን ገቢ ያገኛል::

አርሶአደሩ እንስሳቱን በዘመናዊ መልኩ ለሚያከናወነው የእርባታ ጣቢያ ማስረከቡ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ዶክተር ጌታቸው ይጠቅሳሉ::

ይህም በኋላ ቀር አረባብ የሚደርሰውን የእንስሳት ሞት መጠን በመቀነስ እንዲሁም ለመኖ ፍለጋ እንስሳቱን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በማሰማራት ሲያጠፋ የነበረውን ጊዜና ጉልበት ለሌሎች የልማት ስራዎች እንዲያውል ይጠቅመዋል::

ወጣቶችም በማህበር በመደራጀት ለመኖ ልማት በተመረጡ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ በማልማትና በማዘጋጀት ለእርባታ ጣቢያው እንዲያቀርቡ ማድረግ የፕሮጀክቱ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው::

ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠና በመስጠትና ቁሳቁስ በማቅረብ የስራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ነው የተጠቀሰው::

በፕሮጀክቱ ከታቀፉት ተግባራት መካከል የእንስሳት ጤና መጠበቅና መከላከል ስራዎችም ይገኙበታል:: በተሻሻሉ ዝርያ ከመተካት ባለፈ በእርባታው ለሚታቀፉና ለሌሎች የአካባቢው እንስሳት የክትባትና የህክምና አገልግሎት መስጠትም ያካትታል ።

ከእንስሳቱ የሚገኘውን የስጋና ወተት ምርት በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ የወተትና ስጋ ምርት ማቀነባበርያ ፋብሪካ ማቋቋም ሌላኛው ተግባር መሆኑን ዶክተር ጌታቸው ገልፀዋል::

ለዚህ የልማት ፕሮጀክት አንድ ቢሊዮን ብር በጀት የሚያስፈልግ ሲሆን የአጠቃላይ ወጪውን 60 ከመቶ በአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ይሸፈናል:: ቀሪው ደግሞ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ የሚሟላ ይሆናል ።

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በክሪ እንዳሉት ፕሮጄክቱ ከዚህ ቀደም ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ተጀምሮ ውጤታማ ሆኗል::

ይህንን ልምድ በመቀመርም በምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል::

የምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገና ለመኖ ልማትና ለእንስሳት እርባታ ምቹ መሆን የአካባቢውን አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነም ጠቅሰዋል::

ፕሮጀክቱ የወተት ምርትን በስድስት እጥፍ ፣ የስጋ ምርት ደግሞ በሁለት እጥፍ የሚያሳድግ በመሆኑ ከአካባቢው ባለፈ የሀገር ውስጥ የገበያም ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል ተናግረዋል::

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ በበኩላቸው የመቱ ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክቱን ለማስተባበር መመረጡ በማህበረሰብ አገልግሎት መስኮች ለሚያከናውናቸው ሌሎች ተግባራት ጭምር የበለጠ አቅም እንዲፈጥር ያደርገዋል::

ፕሮጄክቱ በተቀመጠለት ዓላማ መሰረት በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ነው የተናገሩት::

የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ ሁሴን እንዳሉት በፕሮጀክቱ ለሚከናወኑ የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት የሚሆን አመቺ ቦታ በማቅረብ አስተዳደሩ የበኩሉን ይወጣል::

ለልማት ስራው ስኬትም አስፈላጊ በሆኑ መስኮች ሁሉ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል::

የልማት ፕሮጀክቱ የአርሶአደሩን የኢኮኖሚ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የወጣቶችን የስራ ዕድል ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ መቀረፁ የአካባቢውን ልማት እንደሚያፋጥነው የተናገሩት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ ናቸው::

ዩኒቨርሲቲዎቹ ለጀመሩት ተስፋ ሰጪ የልማት ፕሮጀክት የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እንደማይለያቸውና በጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል::

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በተፈጥሮ ሀብት በበለፀገው የደቡብ ምዕራብ አካባቢ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የቀንድ ከብቶች ይገኛሉ።