የሻምበል አበበ ቢቂላ የማራቶን ውድድር የፊታችን እሁድ በሃዋሳ ይካሄዳል

119
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 34ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ የማራቶን ውድድር የፊታችን እሁድ በሃዋሳ ይካሄዳል። የአለማችን መጀመሪያው ጥቁር የማራቶን ውድድር አሸናፊው ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላን በማሰብ በየዓመቱ በሚካሄደው የማራቶን ውድድር ላይ 386 የክለቦችና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች ይሳተፋሉ። ውድድሩ እሁድ ከጠዋቱ ሁለት ሰአት በሀዋሳ ይጀመራል። ከማራቶን ውድድሩ በተጨማሪ ከ50 ዓመት በላይ እና በታች በሚሉ ሁለት ዘርፎች የአንጋፋ አትሌቶች የግማሽ ማራቶን ውድድርም ይካሄዳል። በማራቶን ውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መቀመጫውን በስፔን ባርሴሎና ካደረገው ራነርስ ፎር ኢትዮጵያ ቡድን እና ኢንዶ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ጋር በመሆን ከስፔን የመጡ 25 የፊዚዎቴራፒ ባለሙያዎች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድርም ያደርጋሉ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እሁድ የሚካሄደውን የሻምበል አበበ በቂላ የማራቶን ውድድር አስመልክቶ  ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለጹት የማራቶን ውድድሩ ለክልሎች፣ለክለቦችና ተቋማት እና በግል ለሚወዳደሩ አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫ አማራጭ ውድድሮችን ለመፍጠር ያግዛል። በተጨማሪም ውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለመመልመል ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ሃዋሳ ወደ ቀድሞው መረጋጋቷ በመመለሷ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከደቡብ ክልል መንግስትና ከክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ውድድሩ እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል። የክልሉ የጸጥታ አካላትና የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የማራቶን ውድድሩን ለማካሄድ ሙሉ ኃላፊነት መውሰዳቸውንና ተሳታፊ አትሌቶች በዚህ ላይ ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ገልጸዋል። አትሌቲክስ በአጠቃላይ ስፖርት የአንድነትና የሰላምን መንፈስ የሚሰብክ በመሆኑ ወድድር መካሄዱ በህዝቡ መካከል መቀራረብን ለመፍጠር እንደሚረዳም አቶ ቢልልኝ አስረድተዋል። የኦሮሚያና ደቡብ ክልል እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በውድድሩ ላይ በበጀት ዕጥረት ምክንያት እንደማይሳተፉ ገልጸዋል። ሁለቱ ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለመሳተፋቸው ምክንያት ከባለፈው ዓመት አንጻር የዘንድሮው ተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር በ173 መቀነሱን አስረድተዋል። ከስፔን የመጡት 25 የፊዚዎቴራፒ ባለሙያዎች ከሚያደርጉት የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጡና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የሻምበል አበበ በቂላ ማራቶን ውድድር ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው የሚያስችል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ለቴሌቪዥን ስርጭት የሚያስፈልጉ ትራንስፖንደሮች በመትከል፣ለአትሌቶች በዶላር የመሸለም፣በትራንስፖርት አቅርቦትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማሟላት የማራቶን ውድድሩ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው እንደሚደረግ አክለዋል። በአትሌቲክስ ክለቦችና ተቋማት፣ከሐረሪና ትግራይ ክልሎች፣ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በግላቸው የተመዘገቡ አትሌቶች መካከል በሚደረገው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ30፣ 20 እና 16 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያገኙ ተገልጿል። ከአንድ እስከ አስር ለሚወጡ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት የተዘጋጀ ሲሆን በአጠቃላይ ለዚህ ውድድር 250 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። ከ50 ዓመት በላይ እና በታች በሚሉ ሁለት ዘርፎች በሚካሄደው የአንጋፋ አትሌቶች የግማሽ ማራቶን ውድድር ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ለሚይዙ ተወዳዳሪዎች የ2 ሺህ 500፣ የ1 ሺህ 500 እና የ1 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል። ሻምበል አበበ በቂላ በ1952 ዓ.ም በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አትሌት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በ1956 ዓ.ም በቶኪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም