በድሬዳዋ ሕይወት ያጠፉና ንብረት ያወደሙ አካላትን በህግ ሊጠየቁ ይገባል

126
አዜአ  ኅዳር 7 /2012  መንግሥት በድሬዳዋ ከተማ በሕይወትና ንብረት ጥፋት ያወደሙ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብ ነዋሪዎቿ ጠየቁ። ኅብረተሰቡ ለሰላም ዘብ ከመቆም  አጥፊዎችን ለሕግ አሳልፎ እንዲሰጥ የአስተዳደሩ አመራሮች አሳስበዋል፡፡ የድሬዳዋ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ‘’የሃሳብ ማዕድ’’ በሚል መድረክ  ተሳታፊዎች በከተማዋ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ለጠፋው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ የሆኑ አካላት የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል  ብለዋል፡፡ የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለመመለስና አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡ ወጣት ዮሐንስ አብዲሳ ከተማዋ የሥራ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር የህዝብ ጥያቄዎች ተገን  በማድረግ በቡድን የተደራጁ አካላትና ዘራፊዎች በሚፈፀሙት ወንጀል  ስትታወክ መቆየቷን ይናገራል፡፡ አመራሩ ግልጽነትና ፍትሃዊነትን በተላበሰ መንገድ በመንቀሳቀስ ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል ብሏል፡፡ የሰለጠነ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝና  ሰላምና መረጋጋት እንደሚፈጥር በመግለጽ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዳዊት ታምራት፣ የፌዴራል መንግሥት ሕዝቡ ለከተማዋ የሚጠይቀውን ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን አወቃቀርና ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የህዝቡን ሰላምና ኑሮ እያናጉ፣  ሰው ሰርቶ መብላት የከለከሉ፣ በየቤቱ ደሃውን ሕዝብ ለረሃብ ያጋለጡ አካላትን ለህግ ማቅረብና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈለግ የገለጹት ደግሞ አቶ ሐሰን ዑመር የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ ተመሣሣይ ሃሳብን ያንፀባረቁትና ከዋሂል ቀበሌ የመጡት አቶ መስጠፋ ኑሬ የከተማውን ሰላም ለመመለስ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ይላሉ፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ ከፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ጋር በመቀናጀትና ፈጣን ችሎት በማቋቋም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙትን ተጠርጣሪዎች ቅጣት እንዲያገኙ በመሰራት ላይ ነው ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ በበኩላቸው ከውይይቱ የተገኙ ግብዓቶች ለተጀመረው የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ተግባር ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ጥያቄዎቹን በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም