የኢትዮጵያ የተሻሻለው የንግድ ህግና የንግድ ፖሊሲ በሚቀጥለው ዓመት ስራ ላይ ይውላል-የንግድ ሚኒስቴር

117
አዲስ አበባ ሰኔ13/2010 በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ ስርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የተሻሻለው የንግድ ህግና የንግድ ፖሊሲ  በሚቀጥለው ዓመት ስራ ላይ እንደሚውሉ የንግድ ሚኒስቴር ገለጸ። አገሪቷ የምትምራበት የንግድ ህግ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በ 1952 ዓመት ምህረት የወጣ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ እንደ ግብርናና ገጠር ልማት፣ ጤና ወይም ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ራሱን የቻለ የንግድ ፖሊሲ እንደሌላት ሚኒስቴሩ ገልጿል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የንግድ ህጉ ለብዙ ዓመታት ሳይሻሻል እንደቆየ ገልጸው፤ በተጨማሪም አገሪቷ ራሱን የቻለ የንግድ ፖሊሲ ተግባራዊ ሳታደርግ እንደቆየች ይናገራሉ። ዘመናዊና ቀልጣፋ የንግድ ስርዓት መዘርጋት ባለመቻሉም "በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር አድርጎ ቆይቷል" ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ውጤታማ ለመሆን ራሱን የቻለ የንግድ ፖሊሲ ሊኖራት እንደሚገባ ታምኖበት ጥናቶች ተደርገው ረቂቅ ሰነዱ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። በተመሳሳይ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የወጣው የንግድ ህጉ ዘመኑ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ለመሄድ ውስንነቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተሻሻለው የንግድ ህጉም ሆነ የንግድ ፖሊሲው በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል። ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ 2003 ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲኖረውም ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም