ቢሮው 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እየተረባረበ ነው

68

ህዳር 6 ቀን 2012 የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እየተረባረበ መሆኑን አስታወቀ ።

የቢሮው የገቢ ዕድቅና ጥናት የስራ ሂደት መሪ አቶ አትንኩት በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርስቶች ለማሳካት ካቀደው 3 ነጥብ 9  ቢሊዮን ብር ውስጥ 82 በመቶ የሚሆነውን መሰብሰብ ችሏል ።

ቢሮው የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያነጨውን ገቢ በመሰብሰብ የልማት ወጭን በራስ አቅም ለመሸፈን እየሰራ መሆኑንም የስራ ሒደት መሪው ተናግረዋል ።

በበጀት ዓመቱ ከመደበኛና ከከተማ አገልግሎት ገቢ 14 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ567 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል ።

ገቢን በትትክል አለማሳወቅ፣ ውዝፍ ግብርን በወቅቱ አለመክፈልና ለሸጡት ዕቃና ለሰጡት አገልግሎት ደረሰኝ አለመቁረጥ ዋና ዋና የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ከአቶ አትንኩት በላይ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

ተጠቃሚው ህብረተሰብም ለተገለገለበትና ለገዛው ዕቃ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉ አነስተኛ መሆንና አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ሀሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ግብርን የሚያጭበረብሩበት ሁኔታ መኖር ተጠቃሽ ናቸው።

በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም በግብር ከፋዩ ዘንድ ግብር ለአገር ብልጽግናና እድገት የሚከፈል ዋጋ መሆኑን በትክክል አውቆ የሚጠበቅበትን እንዲከፍል ግንዛቤ በመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

 በተጨማሪም የመስሪያ ቤቱ ተቆጣጣሪዎችና ሙያተኞች የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ በመስራት ህግን ተላልፈው የሚገኙ ግብር ከፋዮችን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በሆቴል ንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ገብሬ ዮሴፍ በሰጡት አስተያየት የደረጃ ሃሌታ "ሀ" ግብር ከፋይ በመሆኔ የተጣለብኝን ግብር በወቅቱ ከፍያለሁ ብለዋል።

የምከፍለው ግብር ለክልሉና ለሀገሪቱ ልማት መፋጠን የሚያበረክተውን ድርሻ በአግባቡ ስለምረዳ የሚጣልብኝን ግብር በየዓመቱ በወቅቱ እከፍላለሁ ሲሉ ተናግረዋል ።

የኤሌክትሪክ ምጣድና ምድጃ ማምረት ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ባንቺአምላክ ያለው በበኩላቸው የተጣለባቸውን ከ24 ሺህ ብር በላይ ግብር በቅርቡ መክፈላቸውን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ "የመስሪያ ካፒታሌ አንድ ሚሊዮን ብር ሳይደርስ ከደረጃ "ሐ" ባለፈው ዓመት ወደ ደረጃ "ሀ" ግብር ከፋይነት እንደድግ መደረጉ ቅሬታ አሳድሮብኛል" ብለዋል።

ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተሰጠኝን ደረጃ እንዲያስተካከል ለተቋሙ ቅሬታ ባቀርብም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በግብር አከፋፈሉ ላይ ጫና አሳድሮብኛል ሲሉም አስረድተዋል።

በክልሉ ከሚገኙ 317 ሺህ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች መካከልም ከ34ሺህ በላይ የሚሆኑት የደረጃ ሃሌታ "ሀ" እና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋይ ነጋዴዎች መሆናቸው ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ቢሮው ባለፈው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቦ ለልማት ስራው እንዲውል ማድረጉን በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም