በወልቂጤ ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ወጣቶች የላቀ ሚና አላቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

84
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 በወልቂጤ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት  የአካባቢው ወጣቶች ቁልፍ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉራጌና ቀቤና ብሄረሰቦች መካከል ባለፈው ሳምንት በተፈጠረው ግጭትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ የተሳተፉ አካላት የማህበራዊ፣ የፖለቲካና የልማት ጥያቄዎችን አንስተው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳብራሩት ሰሞኑን በወልቂጤ ህዝብ የደረሰው ግጭትና ጉዳት "የጉራጌን ህዝብ የማይገልጽ ያልተለመደ ተግባር ነው" ፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ለማንም የማይበጅ አጥፊ በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለይም ወጣቶች ግንባር ቀደም በመሆን ችግሩን በራሳቸው ለመፍታት እንዲጥሩ አሳስበዋል። ባለፉት ጊዜያት የገጠሟቸውን የልማት ፈተናዎች መሰረት በማድረግ ያሉባቸውን የልማት ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት ጥረት ማደረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። የተጀመሩና ቃል የተገቡ የልማት ውጥኖችም በአፋጣኝ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ቃል ገብተዋል። በከተማው የሚካሄዱ የልማት እቅዶች አገርንም፣ ነዋሪውንም ህዝቡንም በእኩልነት በሚጠቅም መንገድ መካሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ግጭቱ በተነሳባቸው የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ቀቤና ዞንና ወረዳዎች ያሉ የበላይ አመራሮች ተገቢውን አመራር ባለመስጠታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን ይለቃሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ ብሔር ተወላጆች እንዲፈናቀሉ ያደረጉ አመራሮችም  እንዲሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቷ የገበያ ስርዓት ፍትሃዊ እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ለሰላሙ መስፈን ላደረጉት አስተዋጽኦና ላደረጉላቸው አቀባበልም  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምሰጋና አቅርበዋል። በውይይቱ  ማብቂያ የጉራጌና ቀቤና ብሄረሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በህዝቡ ፊት ቀርበው ይቅር ተባብለዋል። በወልቂጤ ከተማ ዘላቂ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣትም ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም