የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እየተሰራ ነው

85
ነቀምቴ ኢዜአ ህዳር 06 /2012  በምስራቅ ወለጋ ዞን እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለመሰብሰብ እየተረባረቡ መሆናቸውን ገለፁ ። በምሥራቅ ወለጋ ዞን እያጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በ48 ሺህ 822 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል እንዲሰበሰብ መደረጉን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል  ፡፡ የጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታ አሰበ እንዳሉት አርሶ አደሩ በልማት ቡድንና በደቦ በመደራጀት የበቆሎ፣የሰሊጥ፣የአኩሪ አተር፣የጤፍ፣የቦሎቄና የኦቾሎኒ ሰብሎችን እንዲሰበሰብ አድርጓል ። የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ኪዳነ ያምቦ በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ጭምር አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ያገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በልማት ቡድንና በደቦ በመሰብሰብ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት መረባረብ እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል ። ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር ትምህርት ቤቶች ለተወሰኑ ቀናት ተዘግተው ተማሪዎች በምርት መሰብሰብ ተግባር ተሰማርተው አርሶ አደሩን እንዲያግዙ የማድረግ ሃሳብ መኖሩንም አቶ ኪዳኔ ተናግረዋል ። በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ ከቀጠለ ያልተጠበቀ የምርት ብክነት ሊያስከትል እንደሚችል አንዳንድ የዞኑ አርሶ አደሮች ስጋታቸውን ገልፀዋል ። የጉቶ ጊዳ ወረዳ የመደ ጃለላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደለ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ዝናቡ በተከታታይነት እየጣለ በመሆኑ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ዝናቡ የከፋ ጉዳት እንዳላደረሰ የገለፁት አርሶ አደሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን ብክነት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል ። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዲንቃ ዲሪባ በበኩላቸው ዝናቡ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በደቦ ግማሽ ሄክታር ለውዝ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ የዲጋ ወረዳ የአርጆ ጉደቱ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለታ ቱጌ አንዳሉት ደግሞ እየጣለ ያለው ዝናብ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የበቆሎና የለውዝ ምርቶቻቸውን ለመሰብሰበ በመረባረብ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም