የግብአት አለመሟላትና የመማሪያ ክፍሎች ጥበት በትምህርታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል... በጋምቤላ ተማሪዎች

76
ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2012 የትምህርት ግብዓቶች አለመሟላትና የመማሪያ ክፍሎች ጥበት በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን የጋምቤላ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ፡፡ የክልሉ መንግስት በበኩሉ በትምህርት ቤቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በሂደት ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አንዳንድ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በትምህርት ቤቱ የመማሪያ መጻህፍት፣ ወንበር፣ የቤተ ሙከራና ሌሎችም ግብዓቶች ባለመሟላታቸው በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው ነው፡፡ የመምህራን በበቂ ሁኔታ አለመኖርና የመማሪያ ክፍሎች ጥበት ሌላው ችግር እንደሆነባቸውም ነው የገለጹት። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ተማሪዎች መካከል የ12ኛ ክፍል ተማሪ አስቴር አወቀ እንዳለችው በትምህርት ቤቱ የመማሪያና የማጣቀሻ መጻህፍት እጥረት በመኖሩ በክፍል ውስጥ የተማረችውን ለመከለስ ተቸግራለች፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የወንበር እጥረት በመኖሩ ተጠጋግተው እንደሚቀመጡና ከአካባቢው ሙቀት ጋር ተዳምሮ በመማር ማስተማሩ ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ተናግራለች፡፡ ትምህርት ቤቱ ቤተ ሙከራ ቢኖረውም ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች በመኖራቸው እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ የተናገረችው ደግሞ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ኦሜጋ ኡኮክ ናት፡፡ ይህም በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር ለመስራት ባለመቻላቸው የተፈለገውን እውቀት ማግኘት እንዳልቻሉና ለጤናቸውም ችግር ይፈጥራል የሚል ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው አስረድታለችች፡፡. ሌላዋ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሞላን ታርጃት በበኩሏ በትምህርት ቤቱ በተለይም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች በቤተ ሙከራ ያልታገዙ በመሆናቸው ተጨባጭ እውቀት እያገኙ እንዳልሆነ ነው የገለጸችው፡፡ እስካሁን ድረስ የሒሳብ መምህር ባለመመደቡ የሒሳብ ትምህርት እየተማሩ እንዳልሆነ ተናግራለች፡፡ ተማሪዎቹ እንዳሉት የትምህርት ግብዓቶችና መምህራን አለመሟላታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በላይ ስዩም በበኩላቸው እንዳሉት በዘንድሮው ዓመት ወደመሰናዶ የገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ ይህም በትምህርት ቤቱ የወንበር፣ የመጻህፍትና ሌሎች ግብዓቶች ጋር ተያይዞ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በትምህርት ቤቱ ያለው የተማሪና የመጻህፍት ቁጥር ከፍተኛ ልዩነት የሚታይበት መሆኑን ያመለከቱት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ የማሎ በትምህርት ቤቱ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "በተለይም ከመጻህፍት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን እንዲፈቱ በተከናወኑ ተግባራት ከመጪው ሳምንት ጀምሮ መጻህፍት የማከፋፈል ስራ ይሰራል" ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የወንበር እጥረትን ለመፍታት ከ3 ሺህ 700 በላይ ወንበሮች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ያልተሟሉ መምህራንን ለማሟላትም በአሁኑ ወቅት ቅጥር እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ .የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ትምህርት ቤቱን በቅርቡ በጎበኙበት ወቅት የክልሉ መንግስት የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በከተማዋ ሁለት ተጨማሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መክፈቱን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት የተማሪ ክፍል ጥምርታው ከፍተኛ በመሆኑ የወንበርና የተለያዩ ግብዓቶች ችግር ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኡሞድ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ሲሆን በቀጣይም ይህን ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት የተማሪ ወላጆች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም