በጉባ ወረዳ ማንኩሽ መሰናዶ ትምህርት ቤት ትምህርት ተቋርጧል

119

አሶሳ (ኢዜአ) ሕዳር 06 ቀን 2012  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ በሚገኘው ማንኩሽ መሰናዶ ትምህርት ቤት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ትምህርት መቋረጡን ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

ከመሰናዶ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች መካከል ወጣት ደራርቱ ተመስገን ለኢዜአ እንዳለችው ባለፈው አንድ ወር አብዛኞቹ መምህራን በትምህርት ቤቱ ስለማይገኙ ትምህርት ተስተጓጉሏል፡፡

ይኸው ችግር ተባብሶ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ትምህርት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ተማሪዋ ተናግራለች፡፡

ተማሪ አያና ኢብሳ በበኩሉ ለረጅም ጊዜ ያመለጣቸው ትምህርት በመጪው አገር አቀፍ ፈተናቸው ላይ ጫና ይፈጥርብናል የሚል ስጋት እንዳለው አስረድቷል፡፡

በትምህርት ቤቱ ትምህርት በአግባቡ እየተሰጠ እንዳልሆነና ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮም እየተማሩ እንዳልሆነ ተናግሯል።

የማንኩሽ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አበበ መኮንን በበኩላቸው መምህራን ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ደመወዝ ስለላልተከፈላቸው ትምህርት መቋረጡን አመልክተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጥቅምት ወር 2012ዓ.ም አራት መምህራን ሥራ መልቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

"በጊዜያዊነት የደመወዝ መቋረጥ ችግር ከሁለት ዓመታት በላይ ሆኖታል" የሚሉት ርዕሰ መምህሩ ይህም በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ መምህራንን ማህበራዊ ህይወት በእጅጉ መጉዳቱን ተናግረዋል፡፡

ደመወዝ ባለመከፈሉ ምክንያት መምህራን በትምህርት ቤቱ ባለመገኘታቸው ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ  የመማር ማስተማር ሥራው ሙሉ በሙሉ መቆሙን ርዕሰ መምህሩ አስታውቀዋል፡፡

በመተከል ዞን የጉባ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኩምሳን በወረዳው የማንኩሽ መሰናዶ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በገጠር ቀበሌ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራን ጭምር ደመወዝ በወቅቱ እየተከፈለ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በጤና እና በሌሎች መንግስት ተቋማት ያሉ ሠራተኞች ተመሳሳይ ችግሮች እየገጠማቸው መሆኑንም ነው የገለጹት

"ችግሩን ለክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በተደጋጋሚ አሳውቀናል" ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ቢሮው በጀቱ በቅርቡ እንደሚለቀቅ ቃል መግባቱን አስታውቀዋል።

የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙፍቲ መርቀኒ በበኩላቸው ወረዳዎች የሚላክላቸው በጀት ከትሬዠሪ እና በየወሩ ከሚሰበስቡት ገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉባ ወረዳ ባለፉት ወራት የሚጠበቅበትንገቢ ባለመሰብሰቡሉ በጀት ሳይላክ መዘየቱንምምቱአቶ ሙቲው ለኢአ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሙፍቲ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ቢሮው ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ትናንት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወደወረዳው አካውንት ገቢ አድርጓል።

በእዚህም  የመምህራኑ የጥቅምት ወር ደመወዝ ክፍያ እንደሚካሄድ ነው አቶ ሙፍቲ የገለጹት።

የመስከረም ወር 2012 ዓ.ም. እና ከእዚያ በፊት ያለውን ደመወዝ ያላገኙ የወረዳው ሠራተኞ ካሉ ያቄው ተጣርቶ መፍትሔ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በተከታታይ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በገቢ አሰባሰብ ላይ ጫና መፍጠሩያስታወሱት አቶ ሙፍቲ በእዚህም የበጀት ጉድለት ከስቶት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ወረዳዋች የሚጠበቅባቸውን ገቢ አቅማቸውን አሟጠው በመሰብሰብ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉም መልዕከት አስተላለፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም