አርሶ አደሮች ከኩታ ገጠም እርሻ የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ

77

ነቀምቴ ኢዜአ ህዳር 6 ቀን 2012 በምሥራቅና ቄለም ወለጋ ዞኖች በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከሌላ ጊዜ የበለጠ ምርት እንደሚጠብቁ ተናገሩ ፡፡

ከአርሶ አደሮቹ መካከል በሲቡ ስሬ ወረዳ የቢቂላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደበላ ያደቹ በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸው የሚገኙ  ግንባር ቀደም፣መካከለኛና ድሃ አርሶ አደሮችን በማካተት በክላስተር ተደራጅተው የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ አድርገዋል ።

 በ33 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የዘሩትን በቆሎ በጥሩ ሁኔታ ምርታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በግል በተበጣጠሰ እርሻ በሚያርሱበት ጊዜ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም የአቅም ውስንነት በመኖሩ በቂ ምርት ማግኘት ተስኖአቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በክላስተር ተደራጅተው የኩታ ገጠም እርሻ በመጀመራቸውና አስፈላጊውን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው ቀደም ሲል ከሄክታር ያገኙት የነበረው 40 ኩንታል የበቆሎ ምርት ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ መቻላቸውን ገልፀዋል ።

በግል ከተበጣጠሰ እርሻ በመላቀቅ  በመኽር አዝመራው በክላስተር ተደራጅተው 76 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በቆሎ በማልማት በሄክታር በአማካይ ከ80 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ የተናገሩት ደግሞ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የሜጢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀብታሙ ዴሬሣ ናቸው ፡፡

የኩታ ገጠም እርሻ የሚታረሰው ፣የሚዘራው፣የሚታረመው ፣የግብዓት አጠቃቀሙና የመድኃኒት ርጭቱ የሚካሄደው በተመሳሳይ ወቅቱ በመሆኑ አዋጭነቱ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቄለም ወለጋ ዞን የሰዲ ጫንቃ ወረዳ የመንደር 6 ነዋሪ አርሶ አደር ማንደፍሮ ሲሳይ ናቸው ፡:

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ በኩታ ገጠም እርሻ የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ከግብርና ባለሙያዎች በሚሰጥ የሙያ ድጋፍ የታገዘ በመሆኑ ከሄክታር በ100 እስከ 120 ኩንታል የበቆሎ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል ፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን በመኽር አዝመራው በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 408 ሺህ 417 ሄክታር መሬት ውስጥ 31 ሺህ 768  ሄክታር መሬት በበቆሎ የክላስተር እርሻ መሸፈኑን የዞኑ እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፋንታ አሰበ ከሰጡት ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም