በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ችግር በመፍጠር ጉዳት እንዲደርስ በሚያደርጉ ተማሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል

46
ኢዜአ ህዳር  5/2012 በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ችግር በመፍጠር ጉዳት እንዲደርስ በሚያደርጉ ተማሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስጠንቀቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በዛሬው እለት በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚስተዋለው ችግር ላይ በአገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አመራር አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል። ውይይቱ ያተኮረው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚስተዋሉት ችግሮች መንስኤዎች፣ አስቻይ ሁኔታዎችና መፍትሄዎቹ ላይ ነው። በዚሁ ወቅት የተለያዩ ዩኒቨርስቲ አመራር አባላት በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግጭት ምክንያቶቹ በተለያየ ምክንያት ያኮረፉ፣ ሀገራዊውን ለውጥ ያልተቀበሉ፣ አገሪቱ እንድትረጋጋ ስለማይፈልጉ በዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎችን እንደመሳሪ መጠቀማቸው መሆኑ ተጠቅሷል። ከዚህም ሌላ ኃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሀገር በትክክል እየተመራች አይደለችም የሚል አስተሳሰብ እንዲያዝ ከመፈለግ አኳያ በዚህ ተግባር እየተሰማሩ መሆኑን ለችግሩ ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያና አክቲቪስት በሚባሉ አካላትና እነርሱን የመሰሉ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መልዕክቶችም ግጭቱ እንዲነሳሳ ምክንያት መሆናቸውን ተሳታፊዎች ጠቅሰዋል። የማህበራዊ ሚዲያው መልዕክት እጅግ አፍራሽ በመሆኑ ይህንን የሚፈጽሙት አካላት ላይ ክትትል በማድረግ አስተማሪ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር ቢፈጠር የሚል ሀሳብም ቀርቧል። ግጭቱ እንዲነሳ የሚንቀሳቀሱ አካላትም ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ መዘየድ እንዳለበትም ተነስቷል። ከዚህም ሌላ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሀገራዊ ጉዳዮች በስፋት የሚነሱባቸው ክርክርና ውይይት የሚካሄድባቸው መድረኮች ማድረግ አንዱ መፍትሄ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ከተሳታፊው ቀርቧል። ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ሁኔታዎችን በማጤንና በመተንበይ የመከላከል እርምጃ የሚወሰድበት መንገድም ጠቃሚ መፍትሄ እንደሆነ ተመልክቷል። በዩኒቨርስቲዎችና የፀጥታ አካሉን ጨምሮ ዩኒቨርስቲዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ ቁርኝት መፍጠር ይገባልም ተብሏል። ከዚሁ ጋርም በየአካባቢው በተለያየ እዝ ስር ያሉ የፀጥታ አካላት የተቀናጀ አሰራር እንዲኖራቸውና በአንድ እዝ ስር የሚመሩበት አሰራር መፈጠር እንዳለበትም ሀሳብ ቀርቧል። ዩኒቨርስቲዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮችን በማርገብ ብሎም በመከላከል ረገድ ሊጫወቷቸው የሚችሉ ተግባራትንም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። በአጠቃላይ የፌዴራልና የክልል አመራርን ጨምሮ ዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ፣ የየአካባቢው ነዋሪ ህዝብንና ሌሎች የሚመለከታቸውን በሙሉ ያካተተ ውይይቶችን በማካሄድ ችግሩን ለመፍታት ከወዲሁ ጥረት መጀመር አለበትም ተብሏል። በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋት ከሚስተዋልባቸው መካከል መሆኑን የጠቀሱት የዩኒቨርስቲው ተወካይ ለዚህም የፖለቲካ አመራሩ፣ ዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ፣ የአካባቢው ነዋሪና የአገር ሽማግሌዎች ከታች እስከ ላይ ድረስ መዋቅር በመዘርጋት ሰላማዊ የመማርና ማስተማር ተግባር እውን ይሆን ዘንድ በጋራ በመስራታቸው እንጂ በቂ የፀጥታ ኃይል በአካባቢው በመኖሩ አይደለም ብለዋል። በዩኒቨርስቲው ልዩነትን በማጉላት ለግጭት የሚጋብዙ ሁኔታዎችን ለማጥፋት የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር ችግሩን ለመከላከል እንደሚያግዝም የጅግጂጋ ዩኒቨርስቲው ተሳታፊ ተናግረዋል። በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ  የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ ሀሳቦችና እውቀት የሚንሸራሸርባቸው ሊሆን ሲገባው ሰዎች የሚገደሉበት እየሆኑ መሆኑን ገልፀዋል። ሁኔታውን በመለወጥ ሰላማዊ የመማርና ማስተማር ድባብ ለመፍጠር የሁሉም ማህበረሰብ ትብብር ያስፈልጋልም ብለዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ችግር በመፍጠር ጉዳት እንዲደርስ በሚያደርጉ ተማሪዎች ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቀዋል። የዩኒቨርሲቲዎችን የጥበቃ አቅምን ማዘመን እና አቅም ማሳደግ ይገባልም ብለዋል። በየጊቢው ካሜራ መትከልም ወንጀሉንና ወንጀለኞችን በመለየት ወደህግ ለማቅረብም ያግዛል ሲሉም ጠቅሰዋል። የፌዴራልና የክልል ፀጥታ ኃይላት ከዩኒቨርስቲዎቹ ጋር በመቀናጀት የሰላምና ፀጥታ ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም