የኢትጵያና የቻይና ግንኙነት ለቻይና አፍሪካ ግንኙነት ቀዳሚ ተምሳሌት ነው - በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ

82
ኢዜአ ህዳር 5/2012 የኢትጵያና የቻይና ግንኙነት ለቻይና አፍሪካ ግንኙነት ቀዳሚ ተምሳሌት እንደሆነ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ገለጸ። ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 50ኛ አመት ክብረ በዓል በ2020 ያስቡታል። በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሊ ዩ እንደገለጹት፤ ቻይና ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በትብብር ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህም በተለይ በኢትዮጵያ የተለያዩ እገዛዎችን በገንዘብ፣ በሰው ሃይልና በቴክኒክ እንዲሁም በሌሎችም መንገዶች ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል። ባለፉት አመታትም  የሁለቱ አገሮች መንግስትና ህዝቦች የተቀናጀ ጥረት በንግድና ኢንቨስትመንት የተሻለ ውጤት ሊያመጣ መቻሉን ገልጸዋል። የንግድ የኢንቨስትመንት ግንኙነቱ ወደፊት እየተጠናከረ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት አማካሪዋ ገልጸዋል። ቻይና የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ወንድምና እህት ከማየትም ባሻገር የሁለቱ አገሮች መልካም ግንኙት በተለይ ቻይና በአፍሪካ ለምታደርጋቸው የትብብር መስኮች ተምሳሌት ተደርጎ እንደሚቆጠርም ተናግረዋል። በሚቀጥሉት አመታትም በሁለቱ አገሮች ህዝቦች መካከል ያለው የወዳጅነት ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበትም እገዛዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል። በቀጣይ በመሰረተ ልማት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎችም የትብብር ስራዎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗንም አክለዋል። ሁለቱ አገሮች ባለፉት 50 አመታት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነቶችን መስርተዋል። ቻይና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመላው አፍሪካ ከ43 አገሮች ሰፊ የልማትና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማድረግ የአፍሪካ-ቻይናን ግንኙነቷን እያጠናከረች ትገኛለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም