የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

101

አዲስ አበባ ህዳር 5/2012 በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በ363 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የመንገደኞች ማስተናገጃ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) የተገነባውን የመንገደኞች ማስተናገጃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዛሬ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጎብኝተውታል። የመንገደኞች ማስተናገጃው ዘመኑ የደረሰባቸውን የአየር ማረፊያ መሳሪያዎችና የመንገደኞች አገልግሎት መስጫዎችን ያሟላ ነው። የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ተጠባባቂ ስራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር አለሙ እንደገለፁት፤ የመንገደኞች ማስተናገጃ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ይህም ከዚህ በፊት በማስተናገጃው ይስተዋል የነበረውን የመንገደኞች መጨናነቅና እንግልት የሚያስቀር መሆኑንም አክለዋል። ማስፋፊያው የአየር ማረፊያውን መንገደኞች የማስተናገድ አቅምን በዓመት ከ25 ሚሊዮን በላይ ያሳድገዋል። ማስተናገጃው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ከመሆኑም ባሻገር የመንገደኞችን የማስተናገድ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምረዋል። በ74 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የመንገደኞች ማስተናገጃው በውስጡ የገበያ፣ የመዝናኛ፣ ምግብ ቤቶችና ሌሎችም ተጨማሪ መሰረታዊ አገልግሎት መስጫዎች እንዳሉትም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሊ ዩ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም አቀፍ ደረጃ የአገሪቱ ምልክት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ የመንገደኞች ማስተናገጃ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የአየር መንገዱን አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና አለውም ብለዋል። የተሳፋሪዎችን ቁጥር በመጨመርና የትራንስፖርት አቅሙን ከማሳደጉም ባሻገር የአገሪቱን ብሎም የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል። ከማስፋፊያው በፊት የነበረው ዓመታዊ የአየር ማረፊያው መንገደኞች የማስተናገድ አቅም 7 ሚሊዮን ሲሆን፤ አዲሱ የመንገደኛ ማስተናገጃ ዓመታዊ አቅም ከ25 ሚሊዮን በላይ መሆኑም ተገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ዱባይን በመቅደም ረጅም ርቀት በአየር ላይ ተጉዘው ወደ አፍሪካ የሚገቡ ተጓዦችን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተናገድ ዋነኛ የትራንስፖርት መዳረሻ ነው። የፕሮጀክቱ ግንባታ የተጀመረው በአውሮፓዊያን 2015 እንደነበር ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም